ቀጥታ፡

የቡናን ጥራት በመጠበቅ በገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚሰሩ የቡና አምራቾችና ዩኒየኖች ተናገሩ

ኢዜአ፤ ጥቅምት 19/2012  የቡና ምርታቸውን ጥራት በመጠበቅ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚሰሩ የቡና አምራች አርሶ አደሮችና ዩኒየኖች ተናገሩ፡፡

በቡና ጥራት ማስጠበቅ ዙሪያ ከምሥራቅ፣ምዕራብ፣ቄለም፣ሆሮ ጉዱሩ ወለጋና ምዕራብ ሸዋ ዞን ለተውጣጡ አካላት በግምቢ ከተማ የአንድ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ የለሊስቱ ጉዲና ቀበሌ  ቡና አምራች አንዱ የሆኑት  አርሶ አደር ፈይሣ ገመዳ እንዳሉት፤ ጥራቱን ካለመጠበቅ ጋር ተያይዞ ከቡና ምርታቸው ያገኙት የነበረው ገቢ ዝቅተኛ  ነው።

ከስልጠናው ባገኙት ግንዛቤ ጥራቱን የተጠበቀ ቡና በማምረት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ጥረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

በምዕራብ ወለጋ ዞን የሀሩ ወረዳ ቡና አምራችና አቅራቢ አርሶ አደር መላኩ ተሰማ በበኩላቸው ከሥልጠናው ባገኙት ግንዛቤ ጥራቱ የተጠበቀ ቡና በማምረትና በማዘጋጀት የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በዚሁ ዞን  የጆርጎ ብርብር የገበሬዎች የሕብረት ስራ ዩኒዬን ሥራ አስኪያጅ አቶ ገረመው አፈወርቅ  ቡና አምራች አርሶ አደሮች የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከሚሰጡት ድጋፍ ውስጥ አርሶ አደሩ የደረሰ ቡና እንዲሰበስቡ፣ በአግባቡ እንዲያደርቁና እንዲያከማቹ  የሚያደርጉት የሙያ እገዛን ጠቅሰዋል።

በተመጣጣኝ ዋጋ በመረከብ ጥራቱ የተጠበቀ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪ ለመሆን በአዲስ አበባ መጋዘን ማዘጋጀታቸውንም አመልክተዋል።

የፊድ ዘፊውቼር ኢትዮጵያ ቼይን አክትቪቲ የቡና ቴክኖሎጂ ባለሙያ አቶ ሳዳም ኡመር ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቡና ቅምሻ ውድድር ላይ እንደምትሳተፍ ተናግረዋል።

ባለሙያው እንዳሉት የስልጠናው ዓላማ አርሶ አደሮች የቡና ምርታቸውን በጥራት አምርተው በዓለም ገበያ በተሻለ ዋጋ እንዲሸጡ ለማመቻቸት ነው።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን  ባለሙያ   አቶ ሣህለማርያም ገብረ መድህን በበኩላቸው ኢትዮጵያ በምትሳተፍበት የቡና ቅምሻ ውድድር እንድታሸንፍ ቡና አምራቾች፣አቅራቢዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በስልጠናው ግንዛቤ አግኝተው የድርሻቸውን እንዲወጡ ለመዘጋጀት መሆኑን ተናግረዋል።

የቅድመና ድህረ ምርት አያያዝ ፣ እንዴት ቡናቸውን በጥራት አዘጋጅተው ለውድድሩ መዘጋጀት እንዳለባቸው ከስልጠናው ግንዛቤ እንዲያገኙ መደረጉን አስረድተዋል።

ውድድሩ አርሶ አደሩ በምርቱ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆን፣ የቡና ዓይነቶች ጎልተው እንዲወጡና ለዓለም ገበያ የሚተዋወቁበት ብሎም ሀገሪቱ ከቡና ምርት የምታገኘው ገቢ ከፍ ለማድረግ ጭምር እንደሚያግዝ አመልክተዋል።

በስልጠናው የቡና አምራቾች፣ አቅራቢዎች፣ ዩኒየኖች፣ የወረዳና የዞኑ የቡና ልማት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም