ቀጥታ፡

በአይኦኤም ድጋፍ በ2019 ወደ አገራቸው የተመለሱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ2018 በእጥፍ እንደሚያድግ ተገለጸ

ኢዜአ፤ ጥቅምት  19/2012 በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ድጋፍ በ2019 ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ዜጎች ከ2018 ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ እንደሚያድግ ተጠቆመ።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር  በ2019 በአይኦኤም ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ የስደት ተመላሾች ቁጥር ከዘጠኝ ሺህ በላይ መድረሱም ተመልክቷል።

አይኦኤም እ.አ.አ በ2019 ከአፍሪካ የምስራቅ የስደት መስመር በየወሩ አንድ ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እየተመለሱ መሆኑን ገልጾ፤ ዓመቱ ከገባ ጀምሮ 9 ሺህ 200 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ድጋፍ ማድረጉን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የተጠቀሰው አሀዝ ድርጅቱ እ.አ.አ በ2018 ድጋፍ ካደረገላቸው 5 ሺህ 382 ዜጎች የ3 ሺህ 828 ዜጎች ቁጥር ብልጫ እንዳለው አይኦኤም በዚህ ሳምንት ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል።

በ2019 መጨረሻ ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዜጎች ቁጥር ከ2018 ከነበረው የስደት ተመላሾች ቁጥር በእጥፍ እንደሚያድግ አይኦኤም አስታውቋል።

አብዛኞቹ ድጋፍ የተደረገላቸው የስደት ተመላሾች በተለመዱ የስደት መስመሮች በባህር ዳርቻዎችና ስድተኞችን በሚያጓጉዙ መርከቦች ውስጥ ያለ ምንም ድጋፍ ተትተው የተገኙ መሆናቸውም ታውቋል።

ከተለመዱት የስደት መስመሮች መካከል የአፍሪካ ቀንድን መነሻው አድርጎ ፐርሺያ ባህረ ሰላጤ ዳርቻ ድረስ የሚደርሰው የምስራቅ የስደት መስመር በዋነኛነት እንደሚጠቀስ መግለጫው አመላክቷል።

አብዛኞቹ ስደተኞች አደገኛ የሆነ ጉዞ በማድረግ ራሳቸውን ለከፍተኛ አደጋ እንደሚያጋልጡ የገለጸው አይኦኤም፤ እነዚህ ዜጎች የተለያየ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልጿል።

የፋይናንስ እርዳታ፣ መጠልያና የህክምና ምርመራ እንዲያገኙ፣ የተጠፋፉ ቤተሰቦችን ማገናኘት፣ ታዳጊ ህጻናት ስደተኞች ከወላጆቻቸው ጋር እንዲገናኙ ማድረግ የመሳሰሉ የድህረ ስደት ተመላሾች ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል።

የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ባለፈው ሳምንት 140 ኢትዮጵያውያን ዜጎች ከጅቡቲ በባቡር ወደ አገራቸው በሰላም እንዲመለሱ ማድረጉንም አስታውቋል።

ከተመለሱት አብዛኞቹ ከመጀመሪያውኑ እንዲሰደዱ ባደረጋቸው አስከፊ ሁኔታ እንደሚገኙና አንዳንዶቹ ከመሄዳቸው በፊት በባሰ ሁኔታ ውስጥ እንደሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም የተወሰኑት በእዳ መያዛቸውን እንዲሁም ለጉዞ ብለው ያስቀመጡት ገንዘብ ተሟጦ ማለቁን ድርጅቱ አመልክቷል።

"የሚደረገው የፋይናስ ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ የምናደርገው ድጋፍ ሁልጊዜ ከድህረ ስደት ተመላሾች የተፋጠነ ድጋፍ ባለፈ ዘላቂ የሆነ የማቋቋሚ ስራ መስራት አይቻልም" ያሉት የአይኦኤም የኢትዮጵያ በፈቃደኝነት ለሚመለሱ ድጋፍ እንደገና ማዋሃድና የድንበር አስተዳደር ፕሮግራም አስተባባሪ ሁጎ ጌነስት ናቸው።

ዜጎች በድጋሚ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የሚደረገው ድጋፍ እንደ ድህረ ስደት ተመላሾች ፈጣን ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ስደተኞችን ጨምሮ ዜጎች የተሻለ ህይወት ለማግኘት፣ በግጭት፣ በጭቆና ከህገ ወጥ የሰው ዝውውር ለመዳን ድንበር አቋርጠው የሚያደርጉት ስደት ከፍተኛ ፈተና እንደሆነ ይነገራል።

ከአፍሪካ ቀንድ ብዙ ዜጎች ድንበር አቋርጠው እንደሚሰደዱና ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚያዙ አይኦኤም ይገልጻል።

የመን ጦርነትና በአገሪቷ የተባበሰው የሰብአዊ ቀውስ ሳያግዳቸው በ2019 ወደ የመን የገቡ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ዜጎች ቁጥር እንደጨመረም ተመልክቷል።

በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ግምት በ2019 ወደ የመን የገቡ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ዜጎች ቁጥር 18 ሺህ 500 እንደሆነና አሀዙ ድርጅቱ እ.አ.አ ከ2006 ጀምሮ ወደ የመን የሚገቡ ስደተኞች መረጃ መሰብሰብ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ከፍተኛው ቁጥር እንደሆነ ገልጿል።

ከምስራቅ አፍሪካ አገሮች ወደ የመን ከሚሰደዱት ዜጎች መካከል 60 በመቶ ያህሉ ወጣቶች እንደሆኑና 30 በመቶ ሴቶች 10 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ህጻናት እንደሆኑ መግለጫው አመላክቷል።

አይኦኤም በኢትዮጵያ ለሚያደርገው ድህረ የስደት ተመላሾች ፈጣን ድጋፍ እውን እንዲሆን የዴንማርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የህዝብ የስደተኞችና ስደት ቢሮ የፋይናንስ ድጋፍ ወሳኝ እንደሆነም አክሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም