በሰው ፍጡር ላይ ጉዳት ማድረስ በእስልምና ሃይማኖት የተወገዘ ተግባር ነው - የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
በሰው ፍጡር ላይ ጉዳት ማድረስ በእስልምና ሃይማኖት የተወገዘ ተግባር ነው - የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት
አዲስ አበባ አዜአ ጥቅምት 18 ቀን 2012 በሰው ፍጡር ላይ ጉዳት ማድረስ በእስልምና እምነት ተቀባይነት የሌለውና የተወገዘ ተግባር መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለፀ።
መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበር ተግባር ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም ምክር ቤቱ ጠይቋል።
ምክር ቤቱ ሰሞኑን በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
ሰሞኑን በተከሰተው ችግር ምክንያት የሰው ህይወት በመጥፋቱና ንብረት በመውደሙ እጅግ ማዘናቸውን የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ገልፀዋል።
ለሟች ቤተሰቦችም መጽናናትን ተመኝተዋል፤ በአገሪቱ ሰላምና አንድነት እውን ይሆን ዘንድም ፀልየዋል።
በጠቅላይ ምክር ቤቱ የዑለማዎች ምክር ቤት ፀሐፊ ሼህ ቃሲም መሐመድ ታጁዲን በሰው ልጆች ላይ ጉዳት ማድረስ በእስልምና ሃይማኖት ዘንድ ተቀባይነት የሌለውና ሊፈጸም የማይገባው ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል።
ከግጭቱ ጋር ተያይዞ የተስተዋለው የሃይማኖት ተቋማትን የማቃጠል ተግባር ተቀባይነት የሌለውና ምክር ቤቱ በጽኑ የሚያውግዘው እንደሆነም አመልክተዋል።
የተከሰቱ ችግሮችን በሃይማኖቶች መካከል እንደተከሰተ አድርገው ግጭት ለማባባስ የሚጥሩ አካላትም ከድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው ብለዋል።
መንግስት ሰላምንና የዜጎችን ደህንነት በማስከበር የበኩሉን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።
እያንዳንዱ ዜጋ፣ የሃይማኖት ተቋማትና ሌሎች አካላትም ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት መረጋገጥ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው በማከል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ በበኩላቸው እየተስተዋለ ያለው የጥፋት ተግባር ሊገታ ይገባል ብለዋል።
መንግስትም የህግ የበላይነትን ለማስከበር ተግባር ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ሐጂ ዑመር አክለውም ዜጎች በሰላምና አንድነት ተሳስበው የመኖር የቆየ ባህላቸውን እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።
ወገን በወገኑ ላይ ጉዳት ማድረስ አግባብነት የሌለው ተግባር መሆኑን በመጥቀስ።
የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም በበኩላቸው መንግስት በዜጎች ላይ የደረሰውን ጉዳትና ንብረት መውደም በማጣራት በፍጥነት መረጃውን ለህዝብ ይፋ ማድረግ አለበት ብለዋል።
የሃይማኖት ተቋማትም ከመንግስት ጎን በመሆን የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት በትብብር መስራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።