የኢትዮጵያና አሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ትብብራቸውን ለማጠናከር እየሰሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና አሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ትብብራቸውን ለማጠናከር እየሰሩ ነው
አዲስ አበባ አዜአ ጥቅምት 18 ቀን 2012 የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ያላቸውን የቆየ ትብብር ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑ ተገለጸ።
ከአሜሪካ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበርና ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ጋር መክረዋል።
ከኢትዮጵያ የተሳተፉት የዩኒቨርሲቲ አመራሮች እንደሚሉት የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በተለይ በሰው ሃይል ልማትና በቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የተለያዩ የትምህርት አይነቶችን በጋራ በመስጠትና ለትምህርት ቤት ማደራጃ የሚሆኑ መሳሪያዎችን በማበርከትም የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ይጠቀሳሉ።
በኢትዮጵያ በተለይ በህክምና ዘርፍ ላይ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አመራሮቹ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና እንደገለጹት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ከአሜካ አቻዎቹ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አስታውስዋል።
በአሁኑ ጊዜም ከ20ሚሊዮን ዶላር በላይ ተመድቦ ከ50 በላይ ፕሮጀክቶችን በጋራ ትብብር እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም ይህንኑ ትብብር ለማጠናከር አሁን የተፈጠረው መድረክ ወሳኝ መሆኑን ፕሮፌሰር ጣሰው ተናግረዋል።
የጎንደርና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዝዳንቶችም በየተቋሞቻቸውና በአሜሪካ የትምህርት ተቋማት መካከል የቆየውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
ቀደም ሲል በሰው ሃብት ልማት፣በመምህራንና ተማሪዎች ልምድ ልውውጥና አቅምን የማጎልበት ስራ የተሻለ ትብብር እንደነበራቸውም አንስተዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው የሁለቱ ሀገራት በትምህርት መስክ የቆየ ግንኙነት ቢኖራቸውም በመካከል መቀዛቀዝ አሳይቶ እንደነበር ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ይህንን የቆየ የትብብር ግንኙነት የተሻለ ለማድርግ አሁን ላይ ከሁለቱም አገራት የተሻለ ፍላጎት መኖሩን ገልጸዋል።
ሁለቱ አገሮች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያላቸውን ግንኙነት ለማጠንከር ስምምነት ላይ ደርሰዋል ብለዋል።
የሁለቱ ሀገራት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትብብር መጠናከር ለጋራ ተጠቃሚነት የሚረዳ መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ሂሩት በትብብር ማእቀፉ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መለየታቸውን ገልጸዋል።
የግሎባል ዋን ኤኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተርና የኦሀዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ወንድወሰን ገብረየስ፤ የልኡካን ቡድኑ ከአሜሪካ የተለያዩ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም የልኡካን ቡድኑ በኢትዮጵያ የትምህርት መስክ በትብብር በሚከወኑ ጉዳዮች ላይ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ 50 የመንግስትና የግል ዩኒቨርሲቲዎች ሲኖሩ ከ200 በላይ የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከአሜሪካ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበርና ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የልዑካን ቡድን አባላት አዲስ አበባ የገቡት ከአምስት ቀናት በፊት ነው።
አሜሪካ የቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ዋነኛ የኢትዮጵያ አጋር የነበረች ቢሆንም በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1974 ደርግ ስልጣን ሲይዝ ኢትዮጵያ ወዳጅነቷን ከአሜሪካ ወደ ሩሲያ አዙራ ነበር።
ሆኖም የደርግ መንግስት ወድቆ ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነት እየተሻሻለ መምጣቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።