በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ሙስናንና በመከላከል እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ ደካማ ነው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ሙስናንና በመከላከል እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ ደካማ ነው ተባለ
አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 18/2012 በኢትዮጵያ የሚገኙ የሚዲያ ተቋማት በአገሪቱ የተንሰራፋውን ሙስና በመከላከል መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ ደካማ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ።
ሙስናን ለሚከታተሉ ጋዜጠኞች ከለላ አለመስጠትና የመረጃ እጥረትም የመገናኛ ብዙሃኑ በዘርፉ ደካማ አፈጻጸም እንዲኖራቸው አድርጓል ተብሏል።
መገናኛ ብዙሃን መልካም አስተዳደርን በማስፈንና ሙስናን በመከላከል ረገድ ሊጫወቱት በሚገባው ሚና ላይ የመከረ አውደ ጥናት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዷል።
አውደ ጥናቱን የስነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን እና ቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ለዴሞክራሲ ከተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጀው።
ጋዜጠኞችን ጨምሮ የተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት በተሳተፉበት አውደ ጥናቱ ላይ መገናኛ ብዙሃን ሙስናን በመከላከል ሊኖራቸው የሚገባውን ሚና የሚዳስስ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቧል።
የመገናኛ ብዙሃን፣ ህግና ኮሚኒኬሽን ባለሙያው አቶ ሰለሞን ጎሹ የቀረበው ጥናቱ እንዳረጋገጠው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የሙስናን መንስኤ፣ መገለጫውን፣ ውጤቱንና እያስከተለ ያለውን ጉዳት አስመልክቶ ጥናትን መሰረት አድርገው ትንታኔ በማቅረብ በኩል ድክመት ይታይባቸዋል።
የጸረ-ሙስና ተቋማት በሙስና ትግሉ የሚገባቸውን ሚና አለመጫዎታቸው መገናኛ ብዙሃን ደካማ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው ማድረጉም በጥናቱ ተመልክቷል።
ጥናቱ እንደሚለው አብዛኛዎቹ መገናኛ ብዙሃን ሙስናን በተመለከተ የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች አስፈጻሚው አካል የሚሰጠውን ጥቆማ መሰረት ያደረጉ ናቸው።
የሚዲያ ተቋማት በራሳቸው ተነሳሽነት ከባድ የሙስና ጉዳዮችን በመመርመር የህዝብ አጀንዳ በማድረግ በኩል ውስንነት እንዳለባቸውም በጥናቱ ተጠቅሷል።
የሚወጡ ሪፖርቶችንና ጥቆማዎችን መሰረት አድርጎ እንዲሁም የፖሊስ፣ የአቃቢ ህግ ምርመራዎች ተጀምረው ሲቋረጡ ተከታታይነት ያለው የምርመራ ዘገባ በመስራት በኩል ክፍተት እንዳለ ነው ጥናት አቅራቢው ያብራሩት።
የመንግስት አካላት የምርመራ ዘገባን ከማበረታታት ይልቅ ጉዳዩን "የማዳፈን" ተጽእኖ እንደሚያደርጉ ሪፖርቶችን ጠቅሰዋል የጥናቱ አቅራቡ ገልፀዋል።
አንዳንድ የመንግስት አካላት ሙስናን የሚታገሉ መገናኛ ብዙሃን እንዲጠናከሩ ከማድረግ ይልቅ የማስፈራራት አዝማሚያ ያሳያል፤ ይህም የመገናኛ ብዙሃኑ በጉዳዩ ላይ ደፍረው እዳይሄዱ አድርጓቸዋል ብለዋል።
የፖለቲካ ወገንተኝነት፣ የሃብት እጥረት፣ የጋዜጠኞች ወርሃዊ ክፍያ አነስተኛ መሆን የአቅምና እውቀት ውስንነትንም ለችግሩ ሌሎች ምክንያቶች መሆናቸው በጥናቱ ተመላክቷል።
ችግሮቹን ለማስተካከል ሙስናን በማጋለጥና በጉዳዩ ዙሪያ የዜጎችን ግንዛቤ ማሳደግ ይቻል ዘንድ መንግስት ለጋዜጠኞች በዘርፉ የስልጠና ተቋማትን በማጠናከር አቅም የማጎልበት ተግባር ሊያከናውን እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የመገናኛ ብዙሃን የፖለቲካ ወገንተኝነትን ማጽዳት፣ የመረጃ ነጻነትን ማስፋት፣ በቂ ሃብት መመደብ፣ የጋዜጠኞችን ክፍያ ማሻሻልም ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ጥናት አቅራቢው ተናግረዋል።
የስነ-ምግባርና የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አታክልቲ ግደይ በበኩላቸው የመከላከሉ ተግባር ውጤት ያመጣ ዘንድ መገናኛ ብዙሃን ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህ ጥረት ተቋማቸው አስፈላጊውን መረጃ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳሬክተር አቶ ወንዶሰን አንዱአለም የመገናኛ ብዙሃን ሙስናን በመታገል በኩል የተወሰኑ ጥረቶችና ጅማሮዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ የባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ በማከል።
ለጋዜጠኞች ከለላ አለመስጠት፣ የመረጃ እጥረትና በመንግስት በኩል ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን የመገናኛ ብዙሃን ሚና ደካማ እንዲሆን አድርጎታል ሲሉ ተሳታፊዎች በበኩላቸው አንስተዋል።