አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ያጠናክራል - ባለሃብቶች - ኢዜአ አማርኛ
አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ያጠናክራል - ባለሃብቶች
ጥቅምት 18/2012 አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የግሉን ዘርፍ ተግዳሮቶች በመፍታት 'ተሳትፎውን የሚያጠናክር ነው' ሲሉ ባለሃብቶች ገለጹ። የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ያካተታቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች ''አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ'' በሚል ለባለድርሻ አካላት ለውይይት አቅርቧል። በገንዘብ ሚኒስቴር የፊሲካል ፖሊሲ አማካሪ አቶ ፋንታሁን በለው ባቀረቡት ጽሁፍ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ያስፈለገበትን ምክንያትና ከዚህም ይገኛሉ የተባሉ ውጤቶችን አብራርተዋል። ማሻሻያው የማክሮ ኢኮኖሚውን መዛባት ለማስተካከል፣ መዋቅራዊ ማነቆዎችን ለመፍታትና ሰፊ የስራ ዕድልና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ መዘጋጀቱን አውስተዋል። ለግሉ ዘርፍ የሚሆን የብድር አቅርቦት ውስንነት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ከፍተኛ የዋጋ ንረት የዘርፉ ተዋንያን በሚጠበቀው ልክ እንዳይሳተፉ ማነቆዎች እንደሆኑ ተነስቷል። የሪፎርሙ አጀንዳ በዋናነት ትኩረት የሚያደርገው የተጠቀሱትን ተግዳሮቶች በተቀናጀና ትርጉም ባለው መልኩ ምላሽ ለመስጠት እንደሆነም አቶ ፋንታሁን ገልጸዋል። የግሉ ዘርፍ ባለሃብቶች አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በዘርፉ እያጋጠሙ ያሉትን ማነቆዎች በመፍታት ተሳትፏቸውን ለማጠናከር ትክክለኛው መንገድ እንደሆነ ገልጸዋል። ብሌስ አግሮ ፉድ ፕሮሰሲንግን የወከሉት አቶ ዘላለም ጣሰው የኢኮኖሚ ማሻሻያው እንደ አገር በኢኮኖሚ ፕሮግራም አቅጣጫ የግሉን ዘርፍ ሊደርስበት ከሚገባው ቦታ የሚያደርስ ነው ብለዋል። በተለይ የአገር በቀል የኢኮኖሚ እድገትን ያካተተ መሆኑ ቀልጣፋ የአገር ውስጥ የገበያ ስርዓት እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል። ከኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የመጡት አቶ ሃብታሙ ደሳለኝ በበኩላቸው ቀደም ሲል መንግስት ለአገር ውስጥ ባለሃብቶች የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰው የኢኮኖሚ ማሻሻያው መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ገልጸዋል። ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድንና ቱሪዝም የኢኮኖሚ ማሻሻያው የትኩረት አቅጣጫዎች ሲሆኑ በዘርፎቹም እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት ይሰራል ተብሏል።