አዲሱ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ እያደገ የመጣውን ኢንዱስትሪ ሰላም ከማስጠበቅ አንጻር የጎላ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ እያደገ የመጣውን ኢንዱስትሪ ሰላም ከማስጠበቅ አንጻር የጎላ ሚና አለው
አዲስ አበባ ጥቅምት 18 ቀን 2012 አዲሱ አዋጅ የአሰሪና የሰራተኛን መብትና ጥቅም ከማስጠበቅ ባለፈ እያደገ የመጣውን ኢንዱስትሪ ሰላም ከማስጠበቅ አንጻር የጎላ ሚና እንዳለው የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ። ቀድሞ የነበረው የኢትዮጵያ አሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ሰኔ 30 ቀን በአዋጅ ቁጥር 1156/2011 በአዲስ መተካቱ ይታወሳል። የከተማው ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ይህንን አዋጅ አስመልክቶ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል። የቢሮው የአሰሪና ሰራተኛ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ በዚሁ ወቅት አቶ ተክሌ ዴሬሳ እንዳሉት በቅርቡ የጸደቀው አዋጅ "በህግ ክፍተት ሳቢያ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በበቂ ሁኔታ በመፍታት የኢንዱስትሪውን ሰላም ያስጠብቃል"። የአዋጁ መሻሻልና አዳዲስ ሃሳቦችን አካቶ መምጣት ቀጣይነት ላለው የምርትና ምርታማነት እድገትም ወሳኝ ነው ብለዋል። ቀድሞ በነበረው አዋጅ የሰራተኛውን መብትና ግዴታን ከማስጠበቅ፣ እያደገ የመጣውን ኢንዱስትሪ ሰላም ከማስፈንና ግልጸኝነት ከማረጋገጥ አኳያ ክፍተቶች እንደነበሩበትም አስታውሰዋል ። በተለይም በሰራተኛው የሚነሳውን ቅሬታ በህግ አግባብ ከመፍታት ረገድ ሰፊ ክፍተት ያለበትና ብዙ ጊዜን የሚፈጅ እንደነበር በማውሳት። በሰራተኛውም በኩል የሚታዩ የመቅረትና የማርፈድ ቅጣቶች ገልጽ ባልሆነ መንገድ በመቀመጡ ለአሰራር አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል ብለዋል። አዲሱ አዋጅ ሰራተኛው የሚያነሳቸው ቅሬታዎች ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እልባት እንዲሰጣቸውና ትክክለኛ ውሳኔ እንዲያገኙ ከማድረጉም ባለፈ ግልጽ ያልሆኑ ድንጋጌዎች ለውሳኔ በሚያመች መልኩ ማስቀመጡን ተናግረዋል። በተጨማሪ የሴት ሰራተኞችን መብትና ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻርም አዋጁ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ነው አቶ ተክሌ የተናገሩት። አዋጁ በስራ ቦታና በአካባቢው የማህበራዊ ምክክር ስርዓት እንዲዘረጋና እንዲጠናከርም ምቹና ጤናማ የስራ ከባቢ እንዲፈጠር ያደርጋል ብለዋል። በዚህም የኢንዱስትሪውን ሰላም ዘላቂና ምርታማ ለማድረግና የገበያ ተወዳዳሪነትን አቅም በመፍጠር አገሪቷ ለተያያዘችው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትም እገዛ ያደርጋል ብለዋል። አስፈጻሚዎችም አዋጁን በአግባቡ እንዲተገብሩና የአሰሪና ሰራተኛውን መብት በማስጠበቅ ለአገር ኢኮኖሚ እድገት መደላደል እንዲፈጥሩ አቶ ተክሌ ጠይቀዋል።