የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ልዑካንን አነጋገሩ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ልዑካንን አነጋገሩ
ጥቅምት 18/2012 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የአውሮፓ ኅብረት የፓርላማ ቡድን አባላትን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ የፓርላማ ቡድኑ ከኅብረቱ አምስት የተለያዩ የፖለቲካ ኮሚቴዎች የተውጣጡ 17 አባላትን ያካተተ ነው። የልዑካን ቡድኑ አባላት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ ላይ ተነጋግረዋል። በኢትዮጵያና በአውሮፓ ኅብረት መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮችም መክረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ለሚያደርገው ሁሉን አቀፍ ያልተቋረጠ የልማትና የሰብዓዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። የፓርላማ ቡድኑ አባላት ተከታታይ የኢትዮጵያ ጉብኝትም ኅብረቱ ከአገሪቷ ጋር ያለውን ጠንካራ ግንኘነት ያሳያል ብለዋል። ኅብረቱ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ የአባል አገራቱ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል። ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ለፓርላማ አባላቱ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ ገለጻ አድርገዋል። አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ የተሰሩ ስራዎችን፣ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት በአገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትንም አስረድተዋል። ኢትየጵያ በአፍሪካ ቀንድና በመላ አህጉሪቷ ሠላም እንዲሰፍን እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል። የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች ለማሳካት በሠላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ግንባታ ኢትዮጵያ ለምታደርገው እንቅስቃሴ የአውሮፓ ኅብረት ድጋፉን እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል። የአውሮፓ ኅብረት የፓርላማ ቡድን አባልና የልዑካኑ መሪ ቶማስ ቶቤ የፓርላማ አባላቱ ስራ ከጀመሩ ወዲህ የመጀመሪያ የአፍሪካ ጉብኝታቸው መሆኑን አንስተዋል። ኢትዮጵያ በቀጣናው በተለይም ከኤርትራ ጋር ሠላም ለማስፈን የወሰደችውን ተነሳሽነትና የተገኘውን ውጤትም አድንቀዋል። በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የ2019 የሠላም ኖቤል አሸናፊ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ እድገትና አገሪቱ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ዴሞክራሲ ለመገንባት እያደረገች ያለውንም ጥረት አድንቀዋል። በኢትዮጵያ የተጀመረው ሁሉን አቀፍ ለውጥ ግቡን እንዲመታ የአውሮፓ ኅብረት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም የልዑካን ቡድኑ መሪ አረጋግጠዋል። የልኡካን ቡድኑ አባላት በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የሁለትዮሽ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ለኢዜአ ገልጿል።