በደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ ወረዳ ኩታ ገጠም አስተራረስ የጤፍ ልማትን ውጤታማ አድርጎታል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ ወረዳ ኩታ ገጠም አስተራረስ የጤፍ ልማትን ውጤታማ አድርጎታል
ጥቅምት 18/2012 በደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ ወረዳ በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ በሔክታር የሚገኘው የጤፍ ምርት ከ20 ኩንታል ወደ 30 ኩንታል ማሳደግ እንደተቻለ የወረዳው ግብርና ፅህፈት ቤት ገለፀ ። በደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ ወረዳ በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ የለማውነ የጤፍ ሰብል አቶ ዮሐንስ ቧያለውና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ጉብኝት እየተካሄደ ይገኛል። የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ሃሰን ይማም በጉብኝቱ ወቅት እንደገለፁት በወረዳው በሰብል ከለማው 30 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ግማሽ ያህሉ በጤፍ ሰብል በኩታ ገጠም የለማ ነው። በልማቱ ከ17 ሺህ በላይ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን የተለያዩ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በመጠቀም ልማቱን ማከናወን ተችሏል ። በዚሁ ከለማው መሬት ውስጥም ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ የጤፍ ምርት እንደሚሰበሰብ አቶ ሃሰን አስታውቀዋል። አርሶ አሩ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ በኩታ ገጠም ልማት በስፋት መሳተፍ መቻሉ ምርትና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ጉልህ ሚና መጫወቱን ጠቅሰዋል። ቀደም ሲል በሄክታር እስከ 20 ኩንታል ይገኝ የነበረውም የጤፍ ምርታማነት በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂዎችን በመጠቃም እስከ 30 ኩንታል ማሳደግ መቻሉን አብራርተዋል። በኩታ ገጠም የለማውን የጤፍ ሰብል የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዪሐንስ ቧያለውን ጨምሮ የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መለስ መኮንናና ሌሎች ከፌደራል የመጡ አመራረቶች፣ ባለሙያዎችና የልማቱ የተሳተፉ አርሶ አደሮች ተገኝተዋል። በደቡብ ወሎ ዞን በዚህ የምርት ወቅት በአጠቃላይ 94 ሺህ ሄክታር መሬት በጤፍ ሰብል የለማ ሲሆን ከዚህም 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል።