ቀጥታ፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን ሁለት ግለሰቦች ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውሩ ተያዙ

ኢዜአ ጥቅምት 17/2012፡-  በምእራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ በባጃጅ ተሽከርካሪ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያና መሰል ጥይት ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሁለት ግለሰቦችን እጅ ከፈንጅ መያዙን የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽሕፈት ቤቱ ሀላፊ ዋና ኢንስፔክተር አብራራው የኋላ እንዳስታወቁት ህገ-ወጥ ግለሰቦቹ የተያዙት አንድ ክላሽንኮቭ መሳሪያና 586 ጥይት ይዘው ሲንቀሳቀሱ ትናንት በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ነው። መሳሪያውም ሆነ ጥይቱ ከገንዳ ውኃ ከተማ ወደ መተማ ወረዳ መቃ ቀበሌ ሲጓዝ በጥበቃ ላይ በነበሩ የልዩ ኃይል እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት መያዙንም ተናግረዋል። የባጃጁን መምጣት በመጠባበቅ ላይ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች ሲያዙ ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ለማምለጥ ባደረጉት ሙከራ አንደኛው ህይወቱን ሲያጣ ሌላኛው ለጊዜው ማምለጡን ገልፀዋል። ሁለቱ የተያዙት ግለሰቦች ለህገ-ወጥ ጥይቱ መግዣ የሚውል 54 ሺህ ብር የሚጠጋ ገንዘብ ይዘው መገኘታቸውንም ኃላፊው ተናግረዋል። በዚህ ህገ-ወጥ ተግባር እጃቸው ያለባቸውን አካላት በህግ ጥላ ስር ለማዋል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀው በቀጠናው የሚታየውን ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለመከላከል ከሕብረተሰቡ ጋር በመሆን ጥብቅ የቁጥጥር እና የክትትል ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል። ከሱዳን ጋር በሚያዋስኑ ዋና ዋና መተላለፊያ በሮች ላይም መረጃንና ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ የፀጥታ አካሉና ህብረተሰቡ በመተባበር የክትትል ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። በህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የሚሳተፉ ወንጀለኞችን በማጋለጥና ጥቆማ በመስጠት የአካባቢው ነዋሪ የጀመረውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ዋና ኢንስፔክተሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም