ቀጥታ፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማፋጠን የበለጠ ርብርብ ያስፈልጋል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ጥቅምት 17 /2012 የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማፋጠን የበለጠ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ። በግድቡ ጉዳይ የኢትዮጵያና የግብጽ መሪዎች ሰሞኑን በሩሲያ ያካሄዱትን ውይይት ተከትሎ የቴክኒክ ኮሚቴው ውይይትን ለመቀጠል ከግብጽ በኩል ጥያቄ መቅረቡም ተመልክቷል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ በአዲስ አበባ አካሂዷል። የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሽ በቀለ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ግድቡ ከነበረበት የኤሌክትሮ መካኒካል ስራ ችግር በመውጣት በአሁኑ ወቅት በተገቢው የግንበታ ሂደት ላይ ይገኛል። የኮርቻ ግድቡ ስራ 96 ነጥብ 5 በመቶ የተጠናቀቀ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ አፈጻጸም 68 ነጥብ 53 በመቶ መድረሱን አብራርተዋል። ግንባታው ከዚህ ቀደም ከገጠሙት ችግሮች ወጥቶ በተያዘለት ጊዜ ይጠናቀቅ ዘንድ አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል። ከታችኛው ተፋሰስ አገራት ጋር ያለው የሶስትዮሽ ውይይት በተመለከተ የኢትዮጵያና የግብጽ መሪዎች በሩሲያ ካደረጉት ውይይት በኋላ የቴክኒክ ውይይቱን ለመቀጠል ከግብጽ በኩል ጥያቄ መቅረቡንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በመሆኑም ቀጣዩ የቴክኒካል ኮሚቴው ውይይት በአዲስ አበባ ሊካሄድ እንደሚችል ጠቅሰው፤ ለዛም የግብዣ ደብዳቤ እንደሚላክ አክለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ኢትዮጵያ ግድቡን እየገነባች ያለችው የታችኛው ተፋሰስ አገራት ተጠቃሚነትን በማይጎዳ መልኩ መሆኑን መገናኛ ብዙሃን፣ ምሁራንና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ባገኘው አጋጣሚ እውነታውን ማሳወቅ እንዳለበት አሳስበዋል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከፕሮጀክቱ ውስብስብነትና ግዙፍነት አንጻር የሚፈጠሩ ችግሮችን ከስር ከስር እየፈቱ አለመሄድ ለፕሮጀክቱ መዘግየት በምክንያትነት ጠቅሰዋል። በ2011 በጀት አመት በግድቡ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት ግንባታውን ለማስቀጠል የተከናወነውን ተግባር በማንሳት በተያዘው በጀት አመትም ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ግድቡ እንደ አዲስ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቀደም ሲል ያደርግ የነበረውን አስተዋጽኦ በመቀጠል ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት አመራሮችና አባላት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ህዝብን እንዲያስተባብሩም አሳስበዋል። የህዝቡን ንቅናቄና ፍላጎት እያቀዛቀዘ ያለው አመራሩ በመሆኑ ይህ ይለወጥ ዘንድ በትኩረት እንዲሰራ እንዲሁ። በዛሬው ጉባኤ የ2011 በጀት አመት አፈጻጸምና የ2012 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸም ላይ ተሳታፊዎች ውይይት አድርገውበታል። የህብረተሰቡ ተሳትፎ ተቀዛቅዟል፣ የሚወጡ መረጃዎች የተለያዩ ናቸው የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን በ2015 ዓም ለማጠናቀቅ ነው እየተሰራ ያለው ተብሏል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም