ጽዱ የማብሰል ስርዓትን በመፍጠር የእናቶችን ጤና መጠበቅና የአየር ንብረት ብክለትን መከላከል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ጽዱ የማብሰል ስርዓትን በመፍጠር የእናቶችን ጤና መጠበቅና የአየር ንብረት ብክለትን መከላከል ይገባል
አዲስ አበባ ጥቅምት 17 /2012 ንጽህናው የተጠበቀ ምግብ የማብሰል ስርዓትን በመፍጠር የእናቶችን ጤና ለመጠበቅና የአየር ብክለትን ለመከላከል ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ’የኢትዮጵያ ጽዱ የማብሰል ስርዓት ትብብር’’ ማህበር ገለጸ። በአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስተባባሪነት በጤናና በአየር ንብረት ዙሪያ የሚሰራና ‘’የኢትዮጵያ ጽዱ የማብሰል ስርዓት ትብብር’’ ተብሎ የሚጠራ ማህበር ሰሞኑን መመስርቱ ይታወቃል። ማህበሩ ጽዱ የማብሰል ስርዓትን በመፍጠር የማህበረሰቡን ጤና ለመጠበቅና በአየር ንብረት ላይ የሚደርሰውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመከላከል የተሻሻሉ ተክኖሎጂዎችን ለመጠቀምና ማገዶን ለመቆጠብ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚሰራ ገልጿል። ጽዱ የማብሰል ስርዓት መፍጠር ከሴቶችና ህጻናት፣ ከጤና፣ ከአየር ንብረትና ከኃይል አጠቃቀም ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ስላለውም የሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራትን ይጠይቃልም ተብሏል። የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ከበደ ይማም እንደገለጹት በምግብ አበሳሰል ስርዓቱ ውስጥ አብዛኛው ማህብረሰብ የማገዶ ተጠቃሚ በመሆኑና ከዚህም የሚወጣው የተበከለ ጢስ (ካርቦን ሞኖ ኦክሳይድ) በመሆኑ ለጤና እክል የሚፈጥር ነው። በመሆኑም ይህንን የጤና ችግር ለመከላከል የተሻሻሉ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን በመጠቀም ጽዱ የማብሰል ስርዓት መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል። ይህም ምግብ በሚያበስሉ በተለይም እናቶችን ከሚገጥማቸው የጤና ችግር ያቃልላል ብለዋል። በተጨማሪም ለማገዶ ሲባል የደን ጭፍጨፋን በመቀነስ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስም የራሱ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል። በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ወደ 9 ሚሊዮን የተሻሻሉና ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎች ለማህበረሰቡ መታደሉን ጠቅሰው በሁለተኛው እቅድ ደግሞ 11 ሚሊዮን ለማሰራጨት ታቅዶ እስካሁን እንዳልተሳካና ለዚህም ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ እ.አ.አ በ2011 ነድፋ ወደ ስራ መግባቷንም አስታውሰዋል። በአገሪቷ ለደን መመናመን 46 በመቶ የሚሆነው መንስኤው ለማገዶ ለመጠቀም የሚደረገው ጭፍጨፋ በመሆኑ በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት እየተሰራ ነውም ብለዋል። የማህበሩ ዳሬክተር ዶክተር መኩሪያ አረጋው በበኩላቸው ኃይል ቆጣቢ ባልሆነ ኋላቀርና ክፍት ሶስት ጉልቻ ምድጃዎችን ስንገለገል 90 ከመቶ በላይ የሚሆነዉ የኃይል አገልግሎት ጥቅም ላይ ሳይውል ይቀራል ብለዋል። ይህም ለአገሪቷ የደን ሀብት መመናመን፣ በደን መመናመን ምክንያት ለሚፈጠሩ የአፈር መሸርሸር፣ ለዱር አራዊት ዝርያ መጥፋትና መቀነስ፣ ለአካባቢ አየር መለወጥ፣ ለምርትና ምርታመነት መቀነስ፣ ለሴቶች ጊዜና ጉልበት ብክነት እንዲሁም ለሚከሰተው ጤንነት መንስዔ እየሆነ ይገኛል። ዶክተር መኩሪያ አክለውም አማራጭና ማገዶ ቆጣቢ ቴክኖሎጆዎች አጠቃቀም ላይ በቂ ግንዛቤ ለማሳደግና በዚሁም ጽዱ የማብሰል ስርዓትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችንና ህጎች እንዲወጡና እንዲተገበሩ ግፊትና የማግባባት ስራ ይካሄዳል ብለዋል። እንደ አማራጭም የተሻሻሉ ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎችን፣ አማራጭ የኃይል ምንጭ የሆኑትነውን ባዮጋዝ፣ የፀሐይ ኃይልን እንዲሁም ከተጣሉ ቆሻሻዎች የተሰሩ ከሰልን መጠቀም በትኩረት እንደሚሰራበትም ተናግረዋል።