ቀጥታ፡

የደብር ብርሃን ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎችና ጥያቄዎቻቸው

አዲስ አበባ ጥቅምት 17 /2012  በ2012 የትምህርት ዘመን የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲን ከተቀላቀሉ አዲስ ተማሪዎች መኝታ ክፍሎች መካከል ከአንደኛው ዶርም የተገኘነው በድንገት ነበር። የመኝታ ክፍሉ አባላት እስጢፋኖስ ደረጀ ከአዳማ፣ አያናው ፋሲል ከፍቼ፣ ደራራ በቀለ ከቦረና፣ አላዛር ፈቃዱ ከአዲስ አበባ፣ ደረጃ ብረሃኑ ከደቡብ፣ ግርማ መጣዓለም ከደብረ ወርቅ የመጡ ናቸው። ተማሪዎቹ ስለ ደብረ ብርሃን ምን ተነገራቸው ምንስ ጠበቁ፤ ቀድሞ የነበራቸው ግምትና እውነታው ምን ይመስላል፤ ከጓደኞቻቸው ጋር ያላቸው መላመድስ ምን ይመስላል? የሚሉ ጥያቄዎችን አቀረብን። አንዳንዶቹ እንደጠበቁት አካባቢው ብርዳማ መሆኑን፤ ሌሎቹ ደግሞ የተነገራቸውና ያገኙት እንደማይጣጣም እንዲህ ሲሉ ገልጸውልናል። ተማሪዎቹ በቀጣዮቹ ዓመታት የዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ልዩነቶች ቢኗራቸውም እንኳ እርስ በእርሳቸው ያላቸውን ጓደኝነት በማጠናከር፣ የባህልና የቋንቋ ውርርስ ለማዳበር እንደሚፈልጉም ተናግረዋል። ጠንክሮ ከመማር ባሻገር የመቻቻል፣ የአብሮነት፣ የመከባበርና ለሌሎች ተምሳሌት የመሆን የህይወት እሴቶችን ማዳበር እንደሚገባ ያላቸውን እምነትም ነው የገለጹት። ተማሪዎች ሁለት ሳምንት ባልበለጠ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የታዘቡትና ቢስተካከል ያሉት ዋናው ጉዳይ የምግብ ሲሆን የመጸዳጃ ቤቶች ጽዳትም ሌላው ጥያቄያቸው ነው። የተማሪዎች ሕብረት ሊቀ መንበር አበበ በላይ በበኩሉ የምግብ ግብዓቶች ሲገቡ በኅብረቱ አባላት ቁጥጥር እንደሚደረግና የማይመጥን ከሆነ እንደሚመለስ የማድረግ ስልጣን እንዳላቸው ያብራራል። በምግብ አቅርቦት ረገድ ያለው ያልተፈታው የተማሪዎቸ ጥያቄ ግን እንደ አገር ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ለአንድ ተማሪ የሚበጀተው የ15 ብር በጀት መሆኑን ገልጿል። የጉዳዩ ባለቤት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎችን የቀን በጀት ጉዳይ እንዲያስተካክል ጠየቆ፤ በዩኒቨርሲቲው የምግብ አቅርቦት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከተማሪዎችና ከአስተዳደሩ ጋር በመነጋጋር እንደሚፈቱ አብራርቷል። የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አለባቸው ጎሹ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የምግብ፣ የክሊኒክ፣ የመኝታና የተማሪዎች ጉዳይ በሚሉ አራት ዘርፎች መሰረታዊ አገልግሎት እንደሚሰጥ ይናገራሉ። በዋናነትም በ53 የትምህርት ክፍላት የመጀመሪያ ዲግሪ በሚከታተሉ 12 ሺህ 500 ተማሪዎች መሰረታዊ አገልግሎቶች እንደሚሰጡ ገልጸው፤ ዩኒቨርሲቲውም ለመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤ የሚሆኑ አገልግሎቶችን በበቂ ሁኔታ ለማሟላት ጥረት ማድረጉን ተናግረዋል። በዩኒቨርሲቲው የውሃና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት እጥረት እንደነበር አስታውሰው፤ የውሃ እጥረቱን ለመፍታት ሶስት የከርሰ ምድር ውሃ ቁፋሮ መደረጉን፣ የኤሌክትሪክ መቆራረጥን ለማስቀረት ደግሞ ቀድሞ ከከተማው የሚመጣውን የኤሌክትሪክ ኃይል በቀጥታ ከዋናው መስመር ለዩኒቨርሲቲው ተደራሽ እንዲሆን መደረጉን አውስተዋል። የምግብ ጉዳይ ዩኒቨርሲቲው ከተመሰረተ ጀምሮ ለ13 ዓመታት ተማሪዎች ቅሬታ የሚያነሱበት መሆኑንም ገልጸዋል። ነገር ግን አልፎ አልፎ ከጥራትና ከመጠን ጋር ችግሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉና በተለመደው አሰራር እንደሚስተካከሉ ገልጸው፤ የአዲስ ተማሪዎች ቅሬታ ግን የምግቡን አይነት ካለመላመድ ጋር ተያይዞ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል። ጽዳትን በተመለከተም ዩኒቨርሲቲው በሚያሰራው የጽዳት ማኀበር በኩል ችግሩ እንዲፈታ መደረጉንና ዋናው ችግር ውሃ በመሆኑ ሁሉም የውሃ ጉድጓዶች አገልግሎት ሲሰጡ በሁሉም ህንጻዎች የውሃ አቅርቦት እንደሚኖር ነው የተናገሩት። በሌላ በኩል ከመሰረታዊ አገልግሎቶች ባሻገር የተማሪዎች መዝናኛ፣ የውበት መጠበቂያዎች፣ ተማሪዎች በክፍያ የሚመገቡባቸውን ምግብ ቤቶች በማጠናከር የቅሬታ ምንጭ የሚሆኑ የአቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት እየሰተራ መሆኑንም አስረድተወል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም