ለጌዴኦ ዲላ ስፖርት ክለብ የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለጌዴኦ ዲላ ስፖርት ክለብ የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ
ዲላ (ኢዜአ) ጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ.ም----የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበል አስቻለው ታመነ ለጌዴኦ ዲላ ስፖርት ክለብ የተለያዩ የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡ ድጋፉ ተነሳሽነትን በመፍጠር ክለቡ ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ በኩል አስተዋጾው የጎላ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አንበልና የቅዱስ ጊዮርጊስ የኋላ መስመር ተጫዋች አስቻለው ታመነ ድጋፉን በዲላ ከተማ ተገኝቶ ለክለቡ ባስረከበበት ወቅት እንዳለው ድጋፉን በቅዱስ ጊዮርጊስ አብሮ ከሚጫወተው ጌታነህ ከበደ ጋር በትብብር ያደረጉት መሆኑን ተናግሯል። ለክለቡ እድገትም ሆነ ለስፖርቱ ለውጥ የሁሉም አካል የጋራ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን አመልክቷል። ድጋፉ ለሁለቱም ጾታ የሚሆን የመጫወቻ ጫማ፣ የመለማመጃ ትጥቅ፣ የኳስ እንዲሁም ለስልጠና የሚረዱ ግብዓቶችና መሰል የስፖርት ቁሳቁሶችን ያካተተ ነው፡፡ ለስፖርት ድጋፉ ከ250 ሺህ ብር በላይ ወጭ መደረጉን የገለጸው አስቻለው፣ በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል፡፡ የጌዴኦ ዲላ ስፖርት ክለብ የበላይ ጠባቂና የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ በበኩላቸው ለተደረገው የስፖርት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው መልካም ስራው ለሌሎች ስፖርተኞች አርአያ እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡ በውድድር ዘመኑ የጌዴኦ ዲላ ስፖርት ክለብ ውጤታማ እንዲሆን የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመው ክለቡ ከውጤት በተጨማሪ መልካም ስምና ስፖርታዊ ጨዋነቱን አስጠብቆ መቆየት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ "በቀጣይ በዞኑ ያለውን እምቅ የስፖት አቅም በአግባቡ በመጠቀም አስቻለው ታመነን እና ጌታነህ ከበደን የሚተኩና በአገር አቀፍ ብሎም በዓለም ደረጃ የሚወዳደሩ ስፖርተኞችን ለማፍራት በትኩረት መስራት ይገባል" ብለዋል፡፡ የጌዴኦ ዲላ ስፖርት ክለብ የሁለቱም ጾታ አስልጣኞች በበኩላቸው ድጋፉ ተነሳሽነትን በመፍጠር ክለቡ በውድድር ዘመኑ ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ በኩል የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ በተያዘው የውድድር ዘመን ውጤት ለማስመዝገብ ጠንክረው እንደሚሰሩ የተናገሩት አሰልጠጫኞቹ በተለይ በከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ የሆነውን የወንዶቹ ቡድን ወደ ፕሪሜየርሊግ ለማሳደግ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ የጌዴኦ ዲላ ስፖርት ክለብ በሴቶች በኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ በወንዶች በከፍተኛ ሊግ በመሳተፍ ላይ መሆናቸው ይታወቃል።