ቀጥታ፡

ለሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና እየተሰጠ ነው

ኢዜአ፤ ጥቅምት  17/2012 ለሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና በአዲስ አበባ ተጀመረ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔን ለማከናወን ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አባል ወይዘሪት ብዙወርቅ ከተተ እንደገለጹት፤ ምርጫ ቦርዱ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔን ለማከናወን ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።

ለዚህ ይረዳው ዘንድ እያከናወናቸው ካሉት ዝግጅቶች መካከል ለአስፈጻሚዎች ስልጠና መስጠት ዋነኛው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ የሚሰጠው ስልጠና ከዛሬ ጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት ይቆያል።

ስልጠናው ህዝበ ውሳኔውን ለማስፈጸም የሚያስፈልጉ የህግ ማዕቀፎች፣ የመራጮች የምዝገባ ሂደት፣ የህዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ፣ ቆጠራና ውጤት አገላለጽ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም የህዝበ ውሳኔው ውጤት መገለጹን ተከትሎ የሚነሱ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች የሚፈቱበት ስልትም ሌላው ትኩረት መሆኑም ተመልክቷል።

ስልጠናው የህዝበ ውሳኔ አፈጻጸም የህግ ማዕቀፍ እና ስነ-ምግባር እንዲሁም የድምጽ ቆጠራና የውጤት አዘጋገብ ሂደትን ያካትታል።

የህዝበ ውሳኔ አፈጻጸም ሂደት በተለያዩ የምርጫ ደረጃዎች ማለትም የምርጫ ጣቢያ አደረጃጀት፣ የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባና ድምጽ አሰጣጥ ሂደትም እንዲሁ።

አስፈጻሚዎች ምርጫውን በሰላማዊና በገለልተኝነት መንገድ እንዲያስፈጽሙ አቅማቸውን መገንባትም የስልጠናው ዓላማ መሆኑን ወይዘሪት ብዙወርቅ ጠቁመዋል።

በስልጠናው በአጠቃላይ ከአዲስ አበባና ኦሮሚያ ክልል ለተመለመሉ 6 ሺህ የሚሆኑ አስፈጻሚዎች ሲሆን 30 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።

ከእነዚህም መካከል 5 ሺህ 500 የሚሆኑት በተለያየ ደረጃ ህዝበ ውሳኔውን ለማስፈጸም የሚሰሩ ናቸው ተብሏል። የተቀሩት ደግሞ በተጠባባቂነት ምርጫውን ለማስፈጸም የሚሰለጥኑ መሆናቸውንም ተጠቅሷል።

አስፈፃሚዎቹ የተመለመሉት የማንኛውም ፖለቲካ አባል ያልሆኑ፣ በትምህርት ዝግጅታቸው በማንኛውም የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው፣ እድሜያቸው ከ20 እስከ 40 የሆኑ እንዲሁም በገጠር ቀበሌዎች ተንቀሳቅሰው መስራት የሚችሉ ተብለው በተለዩ መስፈርቶች ነው።

የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ድምጽ መስጫ ቀን ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም ነው።

ህዝበ ውሳኔውን ለማካሄድም በ24 ወረዳዎች 1 ሺህ 692 የምርጫ ጣቢያዎች እና 15 የወረዳ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶች ተዘጋጅተዋል።

በህዝበ ውሳኔው 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ድምጽ ሰጪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም