ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሕንድ መዳረሻውን ወደ ሶስት አሳደገ

ጥቅምት 17/2012 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሕንድ ያለውን መዳረሻ ወደ ሶሰት በማሳደግ ወደ ቤንጋሉሩ በረራ ጀመረ። የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እንዳስታወቁት አየር መንገዱ የህንድ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራዎች ማዕከል ወደ ሆነችው ቤንጋሉሩ በረራውን ጀምሯል።

አየር መንገዱ እስካሁን በዴልሂ እና ሙምባይ ከተሞች በቀን አራት በረራዎች ያሉት ሲሆን አሁን ወደ ቤንጋሉሩ የተጀመረው በረራ ሶስተኛ መዳረሻው መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም በሕንድ ደቡባዊ ከተማ ወደ ሆነችው ቤንጋሉሩ በሳምንት አራት በረራዎች እንደሚኖሩትም አንስተዋል።

አየር መንገዱ እንደ አሮፓዊያን አቆጣጠር ከ1966 ጀምሮ ህንድና አፍሪካን በማገናኘት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የበረራው መጀመር ወደ አፍሪካ፣ ህንድ እና ሌሎችም አካባቢዎች ለሚደረጉ ጉዞዎች አማራጭ እንደሚያሰፋ የጠቆሙት አቶ ተወልደ በቀጣይም በአገሪቱ ቸናይ ከተማም በረራ ለማድረግ ጥናቶች እየተካሔዱ ነው ብለዋል።

ወደ ህንድ የሚደረጉ በረራዎች መጨመር የንግድ የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም ፍሰት እና ትስስርን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተነግሯል።

በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አኑራግ ሲርቫስታቫ በአጭር ጊዜ በረራውን ለመጀመር የተደረገው ጥረት አካል በመሆኔ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።

በረራ መጀመሩ የሁለቱን አገራት የቆየ ታሪካዊ ግንኙት ወደላቀ ደረጃ እንደሚያሳድገው ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመላው ዓለም 125 በአገር ውስጥ ደግሞ 22 መዳረሻዎች አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም