ቀጥታ፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አስተባባሪ ምክር ቤት ጉባኤውን እያካሄደ ነው

ጥቅምት 17/2012 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ጉባኤውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው። የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሚመሩት ጉባኤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት እየተሳተፉ ነው። የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር ያላትን የሶስትዮሽ ውይይትና ግንኙነትን የተመለከተ ገለጻም አድርገዋል። የግድቡ አብዛኛው የኮንክሪት ስራ የተጠናቀቀ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ አጠቃላይ የግንባታ ደረጃውም 68 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን ተናገረዋል። ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በምታደርገው የሶስትዮሽ ውይይት ወቅት ግብጽ የውሃ ሙሌቱን በተመለከተ የተለያዩ ሃሳቦችን እንደምታቀርብ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በሩሲያ ጉብኝታቸው ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር መወያየታቸውን አስታውሰዋል። በውይይታቸውም ከሶስቱ አገራት የተውጣጡት የቴክኒክ ኮሚቴዎች የሚያደርጉትን ውይይት እንዲቀጥሉ መስማማታቸውን አስታውሰዋል። በዛሬው የምክር ቤቱ ጉባኤ በ2011 ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትና 2012 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት ተደርጎ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የስራ መመሪያ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም