የላልይበላ ጎብኚዎች የአካባቢውን የእደ ጥበብ ውጤት እንዲጠቀሙ ለማድረግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የላልይበላ ጎብኚዎች የአካባቢውን የእደ ጥበብ ውጤት እንዲጠቀሙ ለማድረግ እየተሰራ ነው
ጥቅምት 17/2012 በላልይበላ አካባቢ የሚገኙ የእደ ጥበብ ውጤቶች ባህላዊነታቸውን እንደያዙ ደረጃቸውን በማሻሻል ለስራ እድል ፈጠራና ለቱሪዝም ልማት ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ተገለፀ።
የአካባቢውን የእደ ጥበብ ውጤቶችን ለማስተዋወቅ የሚያግዝ የላልይበላ እደ-ጥበባት ፌስቶቫል በከተማው ተካሄዷል።
የከተማው ከንቲባ አቶ ሙሉጌታ ወልደሚካኤል ፌስቲባሉ ሲካሄድ እንዳሉት ላልይበላና አካባቢው ሰፊ የሰው ሰራሽና የፈጥሮ ቅርስ ባለቤት ነው።
በተለይም ዘመናዊ እውቀትና ቴክኖሎጂ እንደ አሁኑ ሳይስፋፋ የአገር ውስጥ እውቀት ስልጣኔ መገለጫ የሆኑ በርካታ የጥበብ ስራዎች ይገኛሉ።
በተለይም ባህላዊ የሆኑ የሸክላ፣ የአልባሳት፣ የብራና፣ የስዕል፣ የቆዳ፣ የእንጨትና ቅርጻ ቅርጽ ስራዎች የላልይበላና አካባቢው አብይ መገለጫዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ የጥበብ ስራዎች በጊዜ ሒደት እየተረሱና የማንነት መገለጫ መሆናቸው እየቀረ የኋላቀርነት ማሳያ ሆነው በመታየታቸው በወጣቱ ትውልድ ዘንድ ሲዘወተሩ አይስተዋልም።
ችግሩን በማጤን ከቅዱስ ላልይበላ ቅርስ ጋር በማስተሳሰር የቀደሙ የእደ ጥበብ ስራዎችን ለቱሪስት በሚመጥን መንገድ ለገበያ እንዲቀርቡ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም አረንጓዴ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ልማት በኢትዮጵያ ፕሮጀክት ተቀርጾ 30 ወጣቶችን በሞዴልነት በማቀፍ ስልጠና በመስጠት ተግባራዊ ስራ ተጀምሯል።
ይህም የእደ ጥበብ ውጤቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ እዲተላለፉ ከማድረግ ባለፈ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ እንዲውል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጅነር መላኩ እዘዘው በበኩላቸው የማንነት መገለጫ የሆኑ የእደ ጥበብ ውጤቶችን ጠብቆ ከትውልድ ትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ሃላፊነት ነው።
የላልይበላና አካባቢው በሃገር ውስጥም ሆነ በአለም ዘንድ ስሙ ሲጠራ ትውስ የሚለው ነገር ቢኖር የስልጣኔና የጥበብ ጫፍ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በመሆኑም በአካባቢው ያለውን የጥንት እውቀት በተሻሻለ አሰራርና ቴክኖሎጂ በመታገዝ ከቱሪዝም ዘርፉ ጋር በማስተሳሰር ለስራ እድል ፈጠራ መጠቀም የግድ ይላል ብለዋል።
አረንጓዴ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ልማት በኢትዮጵያ ፕሮጀክት ከምክር ቤቱ ጋር ተቀናጅቶ በመስራት በላልይበላ የጀመረው ፕሮጀክት የአካባቢውን ተጨባጭ ሁኔታ ማእከል ያደረገና ዘላቂነት ያለው ነው።
የዚህ ፌስቲቫል መዘጋጀትም እውነተኛ ሃገር በቀል የስነ ጥበብ ውጤቶች በማበረታታት የላልይበላ ባህላዊ ቱሪዝሙን ለማበልፀግ የጎላ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።
ይህ ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲሆንና ተሞክረው ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲሰፋ ምክር ቤቱ የድርሻውን እንደሚወጣ ጠቅሰው ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል።
የቀደሙ ባህላዊ የእደ ጥበብ እውቀቶችን በስልጠናና ትምህርት በማገዝ የጥቃቅንና አነስተኛ የስራ ዘርፎች ዘለቄታዊነት እንዲኖራቸው ታስቦ እየተሰራ ነው ያሉት ደግሞ የግሪኒንግ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አስተባባሪ አቶ ሃይሩ ሁሴን ናቸው።
ፕሮጀክቱ በአዲስ አበባና ላሊበላ በሚገኙ 120 የጥቃቅንና አነስተኛ የእደ ጥበብ ኢንተርፕራይዞችን ለ3 ዓመት ታቅፈው ስልጠና አንዲያገኙ በማድረግ ምርቶቻቸውን የማሻሻል ስራ እየተከናወነ ነው።
በቀጣይም በተለያዩ የውጭ ሀገራት ልምድ እንዲወስዱ ይደረጋል ያሉት ስራ አስኪያጁ የተሻለ የፈጠራ ስራ ለሚያቀርቡ ኢንተርፕራይዞችም የገንዘብ ድጋፍ ይደረጋል።
የዚህ ኤግዚቢሽን አላማም በዚህ ወቅት የላልይበላ ቅርሶችን የሚጎበኙ የውጭ ሀጋራት ቱሪስቶች በብዛት የሚመጡበት ወቅት በመሆኑ የገበያ ትስስር መፍጠርና ምርቶችን እውቅና እንዲያገኙ ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል ።
በፕሮጀከቱ ታቅፎ በቆዳ ስራ ውጤቶች የተሰማራወ የላልይበላ ከተማ ነዋሪ ወጣት ታደሰ አሻግሬ በሰጠው አስተያየት ባገኘው ስልጠና ቦርሳ፣ ቀበቶና ሌሎች የቆዳ ውጤቶችን በማምረት ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሷል።
በቋሚነት ምርቶቻቸውን ለገበያ የሚያቀርቡባቸው የመሸጫ ቦታዎች እንዲመቻቹላቸውም ጠይቋል ።
ወይዘሮ አለሚቱ ዘልኡል የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ኤግዚቢሽኑ ባህላዊ የጥጥ ውጤት የሆኑ ጥልፍና ሌሎች አልባሳትን በማቅረብ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ እንዳገዛቸው ተናግረዋል።
ኤግዚቢሽኑን ከጥቅምት 15 እስከ 16 ቀን 2012ዓም ድረስ በነበረው ጊዜ ውስጥ የተካሄደ ሲሆን የላልይበላ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤትና ግሪኒግ ኢትዮጵያ ማንፋክቸሪንግ በጋራ ያዘጋጁት ነው።