ቀጥታ፡

ከመቶ ብር ባነሰ ካፒታል የጀመረነው ቁጠባ ባለሃብቶች አድርጎናል --- የባንክ ደንበኞች

መቐለ ጥቅምት 17/2012 ባለሀብት ለመሆን ቁጠባ ከአሁኑ መጀመር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ከመቶ ብር ባነሰ መነሻ ቁጠባ ጀምረው ሚሊየነሮች ለመሆን የበቁ አንዳንድ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ ።

አቶ ኪዳነ አሰጋኽኝ በመቀሌ ከተማ በወር ከአንድ ሺህ ብር በታች ደመወዝ እየተከፈላቸው ለረጅም ዓመታት በአንድ ሆቴል ሰርተዋል ።

ከ40 ዓመት በፊት በ50 ብር የጀመሩት ቁጠባ በየጊዜው እየጨመረና አማራጭ የስራ እድሎችን እየፈጠረ ዛሬ በኩኋ ከተማ የነዳጅ ማደያ ባለቤት እንዲሆኑ ምክንያት እንደሆናቸው ይናገራሉ ።

በአንድ በኩል እየቆጠቡ በሌላ በኩል ደግሞ ተበድረው እየሰሩ ባለሀብት ለመሆን የበቁት በቁጠባ ሃይል መሆኑን ገልፀው ከማደያው በተጨማሪ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 7 ሚሊዮን ብር ተቀማጭ እንዳላቸው አስረድተዋል ።

ቁጠባን መነሻ በማድረግ የከፈቱት የነዳጅ ማደያ ከራሳቸው ተርፎ ለሌሎች 10 ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠሩንም ተናግረዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ለ8ኛው ዙር እየተከበረ ባለው ''የይቆጥቡ ይሸለሙ ሳምንት'' ምክንያት በማድረግ እንደተናገሩት ''የባንኩ ቁልፍ በእጄ የለም እንጂ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለእኔ ቤቴ ነው'' ባንኩ ባለውለታቸው እንደሆነ ገልፀዋል ።

የነገን የተሻለ ህይወት ለመምራት ዛሬን መቆጠብ አማራጭ የሌለው ከድህነት መውጫ መንገድ መሆኑንም አቶ ኪዳኔ ከራሳቸው ልምድ በመነሳት ሌሎችን ይመክራሉ ።

የመቀሌ ከተማ ወጣት አዜብ ገብረተክለ የቤተሰብ ጥገኛ ከነበረችበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 18 ዓመታት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአቅሟን ያክል እየቆጠበች መምጣቷን ትናገራለች ።

ታዲያ ! በ50 ብር መነሻነት የተቆጠበውን ገንዘብ በማንቀሳቀስና መልሳ የተሻለ በመቆጠብ ሶስት ሚሊዮን ብር የሚገመት የመኖሪያ ቤት ማፍራት እንደቻለች የምትናገረው አዜብ  የቁጠባን ጠቀሜታ ሌሎችንም እንዲከተሉት ትመክራለች  ።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 360 ሺህ ብር ተቀማጭ ጥሬ ገንዘብ ማከማቸት የቻለችው በቁጠባ መሆኑን በመግለፅ ሌሎች ወጣቶችም አርአያነቷ እንዲከተሉ መልእክት አስተላልፋለች።

''የቁጠባ ባህል ማሳደግና ብልህ መሆን ከራስ አልፎ ወገንን የሚጠቅምና ሃገርን የሚገነባ በመሆኑ ሁላችንም ልንከተለው ይገባል'' ብላለች።

ወይዘሮ መአዛ ታፈሰ የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው '' ቁጠባ አንደ ጊዜ ከጀመሩት መልካም ሱስ ነው '' ካሉ በኋላ ሰርተው የሚያገኙትን ትርፍ ገንዘብ ወደ ባንክ በመወርወር ባለፉት ሁለት ዓመታት አንድ ሚሊዮን ብር መቆጠብ እንደቻሉ ተናግረዋል ።

''ገንዘብ የሰዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር መፍቿ ከመሆን ባለፈ ልጆችህ በራስ የመተማመን መንፈስ ይዘው እንዲያድጉ ይረዳል'' ያሉት ወይዘሮዋ ህብረተሰቡ ከብክነት መንገዶች ራሱን ጠብቆ ለቁጠባ ትኩረት እንዲሰጥ ምክራቸውን ለግሰዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቐለ ዲስትሪክት የሃብት ማሰባሰብ ስራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ሰዋሰው ባንኩ በትግራይ ክልል ባሉት 110 ንግድ ባንክ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤቶች 500 ሺህ ደንበኞች እንዳሉት ገልፀዋል ።

በህብረተሰቡ እየታየ ያለውን የቁጠባ ባህል መነሳሳት መነሻ በማድረግ በዘንድሮው ዓመትም 300 ሺህ ተጨማሪ አዳዲስ ደንበኞች ለማፍራት ዲስትሪክቱ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል ።

የደንበኞች ቁጥር ለመጨመር ከሚያስችሉ ስራዎች መካከል ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ሁለት ቅርንጫፎችን ጨምሮ ስምንት ቅርንጫፎች በዘንድሮው ዓመት ይከፍታሉ ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም