በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የቡና ቅምሻ ውድድር ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የቡና ቅምሻ ውድድር ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ ነው
ኢዜአ፤ ጥቅምት 16/2012 በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የቡና ቅምሻ ውድድር ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተሩ ገለጹ። ውድድሩ የዘርፉ ተዋንያን መካከል የውድድር መንፈስ በመፍጠር ከቡና የሚገኘውን ገቢ ያሳድገዋል ተብሏል፡፡ ባለስልጣኑ ትናንት ፊድ ዘ ፊውቸር ቫልዩ ቼይን አክቲቪቲ ከተሰኘ ድርጅት ጋር በውድድሩ አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ውይይት በጅማ ከተማ ተካሂዷል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር አዱኛ ደበላ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ውድድሩ የላቀ ጣዕምና ጥራት ያለው ቡና በማውጣት የተሻለ ገቢ ለማስገኘት ዕድል ይፈጥራል፡፡ ውድድሩም በቡና አምራችነታቸው በታወቁት የአገሪቱ ክፍሎች መካከል ከዚህ ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ እንደሚደረግም አስታውቀዋል። ከፊድ ዘ ፊቸር የቫልዩ ቼን አስተባባሪ ወይዘሪት ቅድስት ሙሉጌታ የውድድሩን ሕግ፣ ደንብና ፋይዳ አስመልክቶ በቡና አብቃይ አካባቢዎች እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ተወካይ አቶ ግዛት ወርቁ በበኩላቸው ውድድሩ የኢትዮጵያ ቡናን ከማስተዋወቁም በላይ አዲስ የገበያ መዳረሻዎች፣የተሻለ ጥራትና ጣዕም ያለው ቡና ለማግኘት፣የገበያ ድርሻን ለማሳደግና በጥራት ለተደራጁ ቡና አምራቾች የተሻለ ይፈጥራል ብለዋል፡፡ ከጅማ ዞን ሊሙ ኮሳ ወረዳ የተሳተፉት አርሶ አደር ሙጃሂድ አባመጫ ውድድሩ በቡና ጥራት ሻምፒዮነትን ለማረጋገጥ ብሎም አሸናፊዎች ከገንዘብ በላይ ለምርታቸው በሚያገኙት እውቅና ገቢያቸውን ለማስፋፋት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡ የጎማ ወረዳው አርሶ አደር ቱጃኔ መሐመድ ውድድሩ የላቀ የቡና ጥራትና ጣዕም እንዳለን ለዓለም ለማሳየት ዕድል ይሰጠናል ብለዋል፡፡ ውድድር በከፍተኛ ደረጃ በሰለጠኑ ባለሙያዎችና በጥንቃቄ ስለሚመራም ዝግጅታቸውንም በዚያው መልኩ ለማድረግ መነሳሳትና እውቅና ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡ ውድድሩን እንደሚያካሂድ የተነገረለት አወዳዳሪው ''አላያንስ ፎር ኮፊ'' ከ20 ዓመታት በፊት የተመሰረተ ሲሆን፣ በ20 አገሮች የቡና ጥራት ቅምሻ ውድድር የሚያዘጋጅ ድርጅት ነው፡፡ በውድድሩ አሸናፊ በሆኑ አገሮች 2ነጥብ 2 ኪሎግራም ቡና ከ300 ዶላር በላይ በሆነ ዋጋ በመሸጥም በተለይ አምራቾችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡