በዓለም ላይ ከፍተኛ የደም አቅርቦት እጥረት እንዳለ አንድ ጥናት አመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም ላይ ከፍተኛ የደም አቅርቦት እጥረት እንዳለ አንድ ጥናት አመለከተ
አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 16/2012 በዓለም ላይ ከፍተኛ የደም አቅርቦት እጥረት እንዳለ አንድ ጥናት አመለከተ።
በጥናቱ መሰረት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለተለያዩ የህክምና ተግባራት ለህይወት አድን ከሚያስፈልገው አጠቃላይ የደም መጠን ውስጥ ከ102 ሚሊዮን ከረጢት በላይ እጥረት አለ።
የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት ከ1 ሺህ ሰው ውስጥ ቢያንስ አስር የሚሆኑት ደም እንዲለግሱ ይጠበቃል።
ሆኖም በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ ደም ከመለገስ ጋር በተያያዘ ያለው ልምድ ዝቅተኛ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል።
በጥናቱ መሰረት ከ195 የዓለም አገራት መካከል በ119ኙ የሚገኙ ሆስፒታሎች ለህይወት አድን የሚያስፈልግ የደም እጥረት የሚስተዋልባቸው ናቸው።
በተለይም በመካከለኛው፣ ምስራቅና የምዕራብ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገራት እንዲሁም ኦሽኒያ (አውስትራሊያን ሳይጨምር)ና ደቡብ ኢዥያ አገራት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ለመታደግ እጅግ ወሳኝ የሆነውን ደም በሚገባው መጠን እየሰበሰቡ እንዳልሆነ የዓለም ጤና ድርጅት አመልክቷል።
መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦች በደም እጥረት ሳቢያ ተገቢ የህክም አገልግሎት ማግኘት እየቻሉ አይደለም ሲል ጥናቱ ይፋ አድርጓል።
እነዚህ የዓለም ክፍሎች በደም እጥረት ምክንያት ወሊድን ጨምሮ ከባድ የቀዶ ጥገና ህክምናዎች ለማድረግ እንደሚቸገሩም ያመለክታል።
በመላው ዓለም በዓመት ከ100 ሚሊዮን በላይ ከረጢት ደም እንደሚሰበሰብ ያሳወቀው ጥናቱ ከዚህም ውስጥ 42 በመቶ የሚሆነው ደም የሚለገሰው ከዓለም ህዝብ 16 በመቶ የሚሆነውን ቁጥር ከያዘው የበለጸጉ አገራት ዜጎች ነው።
ጥናቱ እንደጠቆመው በአፍሪካ አገራት ያለው የደም ልገሳ ልምድ ዝቅተኛ ነው፤ ደም ለመለገስ ከሚመጡት ሰዎች ውስጥም ቢሆን ከደም በሽታ ጋር በተያያዘ ችግር የሚፈለገውን ደም ማግኘት አይቻልም።
በተለይም ደቡብ ሱዳን ያለው የደም ልገሳ መጠን ዝቀተኛ መሆኑን የሚያመለከተው ጥናቱ ከ100 ሺህ ደቡብ ሱዳናዊያን መሰብሰብ የተቻለው 46 ከረጢት ደም ብቻ ነው ብሏል።
በመሆኑም ጥራቱንና ደህንነቱን የተጠበ በቂ ደም መሰብሰብ በሚቻልበት መንገድ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ጥናቱ ያሳስባል።
በተለይም መንግስታት በዚህ ሂደት አስፈላጊውን ድጋፍና ማበረታቻ ሊያደርጉ እንደሚገባ ነው ጥናቱ ያስገነዘበው።
የደም እጥረት ችግሩን ለመከላከል በመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች በመስኩ ኢንቨስትመንስ እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል።
እንዲሁም የደም አስተዳደርን ማጠናከረና አማራጭ የደም ልገሳ ሰልቶችን ማሳደግ እንደሚያስፈልግም ጥናቱ በመፍትሔነት ያስቀመጣል።
በሌላ ዜና ትናንት በመላው ኢትዮጵያ "ደም እንለግስ ህይወት እናድን" በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው የደም ልገሳ መርሃ ግብር ከ14 ሺህ ከረጢት በላይ ደም ተሰብስቧል።
በመርሃ ግብሩ በአንድ ቀን ለመሰብሰብ ተይዞ የነበረው ውጥን 10 ሺህ ከረጢት ነበር።
ሆኖም በእለቱ በተደረገው ደም የማሰባሰብ ዘመቻ ሕብረተሰቡ ባሳየው ከፍተኛ ሰብአዊነት የሚጠበቅበትን ግዴታ በመወጣቱ ከእቅዱ በላይ ደም መሰብሰብ መቻሉን ብሄራዊ የደም ባንክ አስታውቋል።
ከተሰበሰበው ደም በተጨማሪ በእለቱ 22 ሺህ ሰዎች በቋሚነት በየሶስት ወሩ ደም ለመለገስ ቃል ገብተዋል።
በኢትዮጵያ በዓመቱ እየተሰበሰበ ያለው ደም 223 ሺህ ከረጢት ሲሆን በየዓመቱ የሚያስፈልገው ግን አንድ ሚሊዮን ከረጢት ደም ነው።