የሴቶችና ህጻናትን መብት የሚገድቡ የህግ ማእቀፎችን ለማሻሻል ና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ እየሰራሁ ነው … የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችና ህጻናትን መብት የሚገድቡ የህግ ማእቀፎችን ለማሻሻል ና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ እየሰራሁ ነው … የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር
ኢዜአ፤ ጥቅምት 16/2012 የሴቶችና ህጻናት መብትን የሚገድቡ የህግ ማእቀፎችን ለማሻሻልና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ እየተሰራ መሆኑን የሴቶች ህጻናት ና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ እንዳሉት፤ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የ2012 የስራ ዘመን በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ ባቀረቡት የትኩረት አቅጣጫዎች የመንግስትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ና ፖለቲካዊ የስራ እቅዶች የሴቶችን ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ ና ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ናቸው።
በተለይም ልማትን የሚያፋጥኑ የሀይል አቅርቦት፣ የመሰረተ ልማትና በትምህርት መስክ የተሰሩ ስራዎች የሴቶችን ድርብ ጫና በመቀነሳቸው ለሴቶች አቅም መጎልበት ተጨማሪ እድል እንደፈጠረላቸውም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ተጠባባቂ ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ እየሩሳሌም ሰለሞን በበኩላቸው፤ ለውጡን ተከትሎ ሴቶችን በሀገር ልማት ለማሳተፍ የሚደረጉ ጥረቶች የማህበሩን ስራ የሚያግዝ ብቻ ሳይሆን የሴቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎን በማሳደግ ራሳቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ ተጨማሪ አቅም ይሆናል ብለዋል።
የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማደግ የህይወት ልምዳቸውን ከእውቀት ጋር በማጣመር ለሀገር እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እድል ይፈጥራል ያሉት ስራ አስፈጻሚዋ፤ ማህበሩ ባለፉት ሀያ አምስት አመታት ለሴቶችና ህጻናት የነጻ አገልግሎት፣ የአቅም ግንባታ፣ በመብት ጥበቃ ና ጾታ ጥቃትን ለመከላከል የሚያግዙ ግንዛቤን ለህብረተሰቡ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
ሴቶች በሁሉም የስራ መስኮች የሚሳተፉበትና ተጠቃሚ ሚሆኑበትን ስርአት መዘርጋት ያስፈልጋል ያሉት ወይዘሮ ስመኝ፤ ይሄን ተግባራዊ ለማድረግም የአምስት አመት ስትራቴጂ በማውጣት፤ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ለህዝቡ የሚያሰርጹበት አሰራር መፈጠሩንም ነው የተናገሩት።
የሴቶችና ህጻናትን መብት የሚገድቡ አስራር፣ የህግ ማእቀፎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በማጥናት መንግስት እርማት እንዲያደርግ መደረጉን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ እየሩሳሌም ናቸው፡፡
ሴቶች ህግ በማውጣት፣ ህግ በመተርጎም ና በማስፈጸም መሳተፍ መጀመራቸው በመስኩ የሚታዩ የአቅም ክፍተት በመሙላትና ለችግሩ ባላቸው ቅርበት ሌሎችን በማስረዳት ለመፍትሄው መስራት ያስችላልም ነው ያሉት፡፡
የወንዶችን አጋርነት የማበርታትና ወጣት ሴቶች ታላላቆቻቸው ካለፉበት የስኬትና የድክመት መንገድ የሚማሩበት መድረኮች መፈጠሩ፤ እራሳቸውን ከጥቃት ከመከላከል ባለፈ ተጎጂዎች ፈጥነው ህክምና ና ፍትህ እንዲያገኙ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።
አንድ ተቋም ብቻ የሴቶች ጉዳይን ሰርቶ የተፈለገው ውጤት ሊያመጣ ስለማይችል፤ ሁሉም የመንግስት ተቋማት የሴቶችን ጉዳይ አቀናጅተው እንዲሰሩ አቅጣጫ ቢቀመጥም በሚፈለገው መልኩ እየተሰራ አለመሆኑን ነው ወይዘሮ ስመኝ የጠቀሱት።
በሀገሪቱ የሴቶችን መብት የሚደነገጉ ህግጎች ቢወጡም ይህን ማስፈጸም የሚችል ዝርዝር ህግ አለመኖሩ በፍትህ ስርአቱ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን የጠቆሙት ደግሞ ወይዘሮ እየሩሳሌም ናቸው።
ማህበሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ስድት ጽ/ቤት፣ 54 በጎ ፈቃደኞች አስተባባሪ እንዲሁም 360 ኮሚቴዎችን በማሳተፍ የሴቶችን የመብት ጥሰት ለመከላከል እየተሰራ መሆኑንም ነው የማህበሩ ስራ አስፈጻሚ ያስረዱት።