በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ብዝሃነትን በአግባቡ ማስተናገድና ለወቅታዊ ችግሮች መፍትሔ መስጠት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ብዝሃነትን በአግባቡ ማስተናገድና ለወቅታዊ ችግሮች መፍትሔ መስጠት ይገባል
ኢዜአ ጥቅምት 15/2012 ዓ/ም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ብዝሃነትን በአግባቡ ማስተናገድና ለወቅታዊ ችግሮች መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ ተገለጸ። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከ'ኢንሺዬቲቭ አፍሪካ' ጋር በመሆን "በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዘላቂ ሰላም መገንባት" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጁት የባለድርሻ አካላት ምክክር በአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄዷል። በምክክር መድረኩ ላይ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ሃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዘላቂ ሰላም መገንባት የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ የተለያዩ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው በስፋት ውይይት ተደርጎባቸዋል የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶክተር አባተ ጌታሁን ሰላም የሁሉም ነገር ቅድመ ሁኔታ እንደሆነና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ሆነ በኢትዮጵያ ያለ ሰላም ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ የማይታሰብ መሆኑን ተናግረዋል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ተቋማቱ ኢትዮጵያ ያላትን ብዝሃነት ማስተናገድ መቻል እንዳለባቸው ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሌሎች አገራት በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳለው ብዝሃነት የሚስተናገድበት የአሰራር መመሪያና ፖሊሲ ሊኖራቸው እንደሚገባም አመልክተዋል። የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች የኢትዮጵያ አጠቃላይ ነጸብራቅ በመሆናቸው ብዝሃነትን ማስተናገድ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ ነው ብለዋል። በዩኒቨርሲቲዎች እርስ በእርስ የመደማመጥና የመግባባት ባህል ሊዳብር እንደሚገባና ለዚህም ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል። የጅንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ገብሬ ኢቲሶም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላም እንዲኖር ለማድረግ የውስጥ ችግሮችን መፍታት ብቻ በቂ ባለመሆኑ "ለውጫዊ ችግሮችም መፍትሄ መስጠት ይገባል" ብለዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በዩኒቨርሲቲዎች የጸጥታ ችግሮች ሲከሰቱ በጅንካ ዩኒቨርሲቲ ምንም አይነት ችግር እንዳልተፈጠረና ይህም የሆነው በከተማዋ የነበረው ሁኔታ ሰላማዊ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ለአብነት አንስተዋል። የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቀነኣ ያደታ በዩኒቨርሲቲዎች ሰላም እንዲረጋገጥ ለችግሮቹ መነሻ የሆኑ ምክንያቶችን "ከስሩ ለይቶ የመስራት ተግባር እየተከናወነ ነው" ብለዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ከፖለቲካ፣ ሃይማኖትና ሌሎች የግል ሀሳቦች የሚንጸበረቁባቸው ሳይሆን ነገ ኢትዮጵያን የሚረከቡ ዜጎች መፍለቂያ እንዲሆኑ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንዳሉትም የምክክር መድረኩ ዓላማ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ለሚፈጠሩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ በመስጠት ሰላም ማስፈን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያያት እንደሆነ ጠቅሰዋል። የሚታሰበውን ዘላቂ ሰላም ለማስፈንም በዋነኛነት ኢትዮጵያዊነት የተላበሰ የዩኒቨርሲቲ ባህል መገንባት እንደሚያስፈልግና ለዚህም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተሳካ የመማር ማስተማር እና የምርምር ስራዎችን ለማከናወን ሰላማዊ የሆነ የትምህርት ካባቢ እጅግ አስፈላጊ ነውም ብለዋል። ለዚህም ሚኒስቴሩ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። ባለፉት ዓመታት በዩኒቨርሲቲዎች የነበሩ ግጭቶችና ሁከቶች ዳግም እንዳይከሰቱና ሰላማዊ የትምህርት ሂደት እንዲኖር ሁሉም አካል ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።