ቀጥታ፡

በትግራይ 2 ሺህ 700 ወጣቶች የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል ወደ ቦታው ተንቀሳቅሰዋል

ማይጨው/መቀሌ/ኢዜአ ጥቅምት 15/12 ዓ/ም በራያ አዘቦና በራያ አላማጣ ወረዳዎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ከመቀሌና ከዓዲግራት አካባቢዎች 2 ሺህ 700 ወጣቶች ወደ ስፍራው መጓዛቸውን የትግራይ ወጣቶች ማህበር ገለፀ ። የትግራይ ወጣቶች ማህበር ምክትል ስራ አስኪያጅ ወጣት ጌታቸው ለገሰ እንደገለፀው ወጣቶቹ ከወረዳዎቹ አርሶ አደሮችና ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን መንጋውን ለማጥፋት በ45 አውቶቡሶች ዛሬ ወደ ቦታው ተንቀሳቅሰዋል ። በመቀሌ ዩኒቨርስቲ እና በመቀሌ 70 እንደርታ እግር ኳስ ክለብ አስተባባሪነት ወደ ዘመቻው የተሰማሩ 2 ሺህ 700 ወጣቶች የአንበጣ መንጋውን ከራያ ምድር እስኪጠፋ ድረስ እገዛ ያደርጋሉ። የአንበጣ መንጋው በአፋርና በቆቦ በኩል ወደ ራያ አዘቦና ራያ አላማጣ ወረዳዎች ዘልቆ መግባቱንና ወደ ሌሎች ወረዳዎች እየተዛመተ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የደቡባዊ ዞን ግብርናና ገጠር ልማት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ አሰፋ አስረስ ናቸው ። ከጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ  ኡላጋ፣ መቻሬ፣ ኮርማና አርባ በተባሉ አካባቢዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ አሁን ላይ ቁጥሩን እየጨመረ በሁሉም የራያ አዘቦ ቀበሌዎችና በራያ አላማጣ ወረዳ ልዩ ስሙ ለምለም በተባለ ቀበሌ ድረስ መዛመቱን ገልጸዋል። የአንበጣ መንጋው እስከ አሁን ድረስ በአዝርእት ላይ ጉዳት ባያደርስም ከወዲሁ ካልተወገደ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል የሚል ስጋት ማሳደሩን አቶ አሰፋ ተናግረዋል ። በባለሙያዎች የተደገፈ ጥብቅ ክትትል በማድረግ የአንበጣ መንጋው ማሳ ውስጥ እንዳያድር በማድረግ ባረፈበት  ቦታ ሁሉ የኬሚካል ርጭት እየተካሔደ ነው ብለዋል ። በቁጥጥር ስር ለማዋል አስቸጋሪ እየሆነ በመምጣቱ ከሌላ ቦታ ተጨማሪ የሰው ኃይል እንዲመጣ መደረጉንም አያይዘው ገልፀዋል ። በራያ አዘቦ ወረዳ የካራሽሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቦሩ ሀፍቱ እንደገለፁት የአንበጣ መንጋው ወደ ቀያችን ከገባ ጀምሮ ማሳችን እንዳያጠቃ እየተከላከልን እንገኛለን ብለዋል ። ጅራፍ በማጮህና በመጨፍጨፍ የመከላከል ስራ እያከናወንን ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ መንጋውን መቆጣጠር እንዳልተቻለ አስረድተዋል ። መንግስት የጀመረው የኬሚካል ርጭት አጠናክሮ እንዲቀጥልም አርሶ አደሩ ጠይቀዋል ። አቶ አባዲ ኪሮስ የተባሉ አርሶ አደር እንደገለፁት ደግሞ አንበጣውን እስከ አሁን ድረስ በአዝርእት ላይ ጉዳት ባያደርስም ስጋታችን ግን ከፍተኛ ነው ብለዋል። ቀን ከሌሊት ማሳቸውን በመጠበቅ ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ አባዲ አንበጣውን ለመቆጣጠር ተጨማሪ ርብርብ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
   
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም