ቀጥታ፡

በአዳማ ከተማ በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት የሆኑ አካላት ተለይተው ለህግ እንዲቀርቡ ተጠየቀ

አዳማ ኢዜአ ጥቅምት 14/2012፡- በአዳማ ከተማ የጸጥታ ችግር በመፍጠር በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት የሆኑ አካላት ተለይተው ለህግ እንዲቀርቡ በከተማዋ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ጠየቁ። ከወጣቶቹ መካከል ነጻነት ለማ እንዳለው አዳማ በሰላም የምትታወቅ ከተማ ከመሆኗም ባለፈ ለሌሎች የክልሉ ከተሞች ተምሳሌት ናት። “ባለፉት ዓመታት በዙሪያዋ ችግር ሲፈጠር የአዳማ ህዝብ በሰላም አብሮ ሲኖር ነበር “ያለው ወጣት ነጻነት አሁን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የተፈጠረው ችግር አሳፋሪ መሆኑን ገልጿል ችግሩን የፈጠሩይ ከሌሎች ቦታ ተልኮ ይዘው የመጡ የራሳቸውን አጀንዳ በከተማ ነዋሪዎች ላይ በኃይል ለመጫን የሚጥሩ አካላት ተላላኪ እንደሆኑ ተናግሯል። “እናቶቻችንና አባቶቻችን ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ በሰላም ወጥቶ ለመግባት እንዲቻል አሁን የተፈጠረው ድርጊት ከመሰረቱ መወገድ አለበት” ብሏል። ለዚህም የከተማ ነዋሪ ህብረተሰብ ከመንግስት ጎን ቆሞ ጥፋተኞችን በማጋለጥ ለህግ ማቅረብ እንደሚገባ አመልክቷል ወጣት ነጻነት “የከተማው ወጣቶች መስራት ፣መለወጥና በሰላም አብሮ መኖር የሚፈልጉ በመሆናቸው ይህንን ችግር የፈጠሩ አካላት የማናውቃቸውና አዲስ ፊት ናቸው “ብሏል። መንግስት በአስቸኳይ በጉዳዩ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑና ከጀርባ ሆኖ በመግፋት ለሰው ህይወትና ንብረት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ጥፋተኞች ተለይተው ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቋል። “ወጣቱ ጥፋተኞችን በማጋለጥ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ለሰላም ዘብ መቆም አለበት” ያለው ደግሞ ወጣት ቢኒያም ታደሰ ነው። ሁከትና ግርግር በመፍጠር የሰው ህይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም ያደረጉት አካላት በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ሳይሆኑ ከሌላ ቦታ የመጡ የጥፋት ተላላኪዎች እንደሆኑም ተናግሯል። “የተፈፀመው ድርጊት በቡድን ሰው በማጥቃት ፣በዝርፊያና በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ድርሷል “ያለው ወጣት ጥፋተኞች ተጠርተው በህግ ሊጠየቁ እንደሚገባ አመልክቷል። ችግሩ ሳይሰፋና የከፋ ጉዳት ሳያስከትል ህዝቡ ከፀጥታ ኃይል ጋር በመሆን ሁከትና ግርግሩ በቁጥጥር ስር መዋል መቻሉ እንዳስደሰተው ተናግሯል። ወጣት ተሻለ ቱራ በበኩሉ “ወጣቱም ሆነ ሌላውም ነዋሪ በስሜት ከመነዳት ይልቅ ጥቅምና ጉዳት በመመዘን በሰላማዊ መንገድ ሃሳባችንን መግለጽ እንችላለን “ ሲል ገልጿል። ህብረተሰቡም በተለየም ወጣቱ የግል ፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ መሳሪያ መሆን እንደሌለበትም ጠቁሟል። በችግሩ የተሳተፉትን አካላት በመለየት በመንግስት ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸውም ጠይቋል። ወጣቱ እንዳመለከተው የነበረው ሁኔታ ሃሳብን በነጻናት በሰላማዊ መንገድ መግለፅ ሳይሆን ጎራ ለይቶ አንዱ በአንዱ ላይ የበላይነት ለመያዝ የተደረገ እንቅስቃሴ ተገቢነት የለውም። “የከተማዋን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስና አስተማማኝ ለማድረግ የፀጥታ አካላትን ማገዝና መተባበር ይጠበቅብናል” ብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም