ቀጥታ፡

አየርላንድ ለምርታማ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር 10 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ድጋፍ ልታደርግ ነው

ጥቅምት 14/2012 የአየርላንድ መንግስት ለምርታማ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር የሚውል 10 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ልታደርግ ነው። የገንዘብ ድጋፉ ከህዳር ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚለቀቅም ተገልጿል። ስምምነቱን የተፈራረሙት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ አድማሱ ነበበ እና የአየርላንድ ዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ኤጀንሲ (አይሪሽ ኤድ) ኢትዮጵያ ሃላፊ ፓትሪክ ማክማነስ ናቸው። የምርታማ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር ምዕራፍ አራት እ.አ.አ ከ2015 እስከ 2020 ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን የአየርላንድ መንግስት ድጋፍ ለመር ሃብሩ የ2019/20 ማስፈጸሚያ የሚውል ነው። የምርታማ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር በድርቅ የተጎዱና በዝቅተኛ ኑሮ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ በኑሯቸው ለውጥ እንዲያመጡ የታሰበም ነው ተብሏል። የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ አድማሱ ነበበ ድጋፉ የምግብ ዋስትናቸውን ያላረጋገጡና በድርቅ የተጎዱ ዜጎች ኑሮን በማሻሻል የዜጎችን የአደጋ መቋቋም አቅም ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነውም ብለዋል። ዜጎች በዘላቂነት የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰሩ ላሉ ስራዎች እንደሚውልም ገልጸዋል። በተጨማሪም ዜጎች በገጠር የሴፍቲኔት መርሃ ግብር ያላቸውን ተጠቃሚነት እንዲያሳድግ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል። ዜጎች በምርታማነት ሴፍቲኔት መርሃ ግብር ከሚደረግላቸው ድጋፍና ከሚያገኙት አገልግሎት ባለፈ በዘላቂነት ኑሯቸው እንዲሻሻል እንደሚሰራም አመልክተዋል። የምርታማ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር እ.አ.አ ከ2005 ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንና እስካሁን በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና በሰባት ክልሎች ውስጥ 382 ወረዳዎች የሚገኙ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ነው አቶ አድማሱ ያስረዱት። የአየርላንድ መንግስት ድጋፍ በምዕራፍ አራት የመርሃግብሩ የመጨረሻ ዓመት ትግበራ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ አጠቃላይ የመርሃ ግብሩን ተጠቃሚ ወደ 7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች ያሳድጋልም ብለዋል። አየርላንድ የምታደርገው ድጋፍ ለታለመለት አላማ እንዲውልም መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሰራና አየርላንድ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል። ኢትዮጵያና አየርላንድ በፖለቲካና በኢኮኖሚው መስክ ጠንካራ ትብብር እንዳላቸውና የዛሬውም የድጋፍ ስምምነት ይሄንኑ ትብብር ይበልጥ የሚያጎለብት እንደሆነም አክለዋል። የአየርላንድ ዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ኤጀንሲ (አይሪሽ ኤድ) የኢትዮጵያ ሃላፊ ፓትሪክ ማክማነስ አየርላንድ የምርታማ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር ተግባራዊ ከሆነ ጊዜ አንስቶ ድጋፍ እያደረገች መሆኑን አውስተዋል። መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያና የአየርላንድ የልማት ትብብርና አገራቱ ያላቸው ግንኙነት ዋነኛ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ እንደሆነም ገልጸዋል። መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያ የማህበራዊ ዋስትና መርሃ ግብር እንደሆነና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው እንዲሁም አርአያ የሚሆን መሆኑን ገልጸው አየርላንድና ሌሎች አገራት ትምህርት የቀሰሙበት ነውም ብለዋል። የግብርና ሚኒስቴርና ሌሎች አካላት መርሃ ግብሩ የታለመለትን ግብ እንዲያሳካ እየሰራ ያለው ስራ መርሃ ግብሩን ውጤታማ እንዲሆን እንዳደረገውም ነው ሚስተር ፓትሪክ ያስረዱት። በአየር ንብረት ለውጥ የሚደርሱ አደጋዎች ዜጎች እንዲቋቋሙም መርሃ ግብሩ ወሳኝ ሚና እንዳለውም ጠቅሰዋል። በቀጣይም መርሃ ግብሩ ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል የአየርላንድ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። በተያያዘ የአየርላንድ መንግስት እ.አ.አ ከ2020 ጀምሮ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አስመልክቶ ስትራቴጂ እያዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል። ስትራቴጂው ይፋ የሚደረግበት ዓመት የምርታማ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር ምዕራፍ አምስት ትግበራ ጅማሬ እንደሚሆንና ይህም ጊዜውን የጠበቀ እንደሆነ ጠቅሰዋል። መንግስታቸው በቀጣይ አምስት ስድስት ዓመታት ለኢትዮጵያ ልማት የሚያደርገውን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያሳድግም ነው ሚስተር ፓትሪክ የጠቆሙት። ኢትዮጵያ የአየርላንድ የልማት ድጋፍ ተጠቃሚ ከሆኑ አገራት ዋነኛዋ እንደሆነችና ይሄም በቀጣይ ጊዜያት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል። የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተመለከትም የአየርላንድ መንግስት በአዲሱ ስትራቴጂው ማሻሻያው የድጋፉ አካል በሚሆንበት ሁኔታ ጋር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ውይይት እንደሚያደርግም አክለዋል። ኢትዮጵያና አየርላንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1994 ሲሆን ሁለቱም አገራት በየአገራቱ ኤምባሲያቸውን ከፍተው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ። የአየርላንድ ዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ኤጀንሲ(አይሪሽ ኤድ) ለኢትዮጵያ የሚያደርገው ድጋፍ በድህነት ቅነሳ እና የኢኮኖሚ እድገት ላይ ያተኮረ ነው። የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ጤና፣ የንጽህና አጠባበቅ፣ የምግብ ዋስትና፣ ሰብአዊ ጉዳዮችና ጾታዊ ጥቃትን መከላከል የልማት ተራድኦው በኢትዮጵያ ድጋፍ ከሚያደርግባቸው መስኮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም