በሐረር ሰላምና መረጋጋት እየሰፈነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሐረር ሰላምና መረጋጋት እየሰፈነ ነው
ሐረር ጥቅምት 14 ቀን 2012 በሐረር ከተማና አካባቢው ሰላምና መረጋጋት በመስፈን ላይ ነው። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር እንደታዘበው ላለፉት ሁለት ቀናት የነበረው ውጥረት ጋብ ብሎ ሕይወት መደበኛ መሥመሯን መያዝ ጀምራለች። በከተማዋ በነዚህ ቀናት በነበረው ግጭት በሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። የከተማዋ የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ጀምሯል። እንዲሁም ከሐረር - ጅግጅጋ የትራንስፖርት እንቅሰቃሴ መጀመሩንም ተመልክቷል። ሆኖም የመንግሥት ተቋማት ፣ ባንኮችና ሌሎች ከፍተኛ የንግድ ተቋማት ሥራ አልጀመሩም። አቶ አቢ ደረጀ የተባሉ አሽከርካሪ በሰጡት አስተያየት ከሐረር ወደ ጭሮ መንገድ በመከፈቱ መንገደኞችን አሳፍረው እየተጓዙ መሆናቸውን ገልጸዋል። ወይዘሮ ሰዓዳ ዓሊ የተባሉ ነዋሪ መንግሥት በየጊዜው በሚፈጠሩ ግጭቶች እየጠፋ ያለውን ሕይወትና ንብረት ለመታደግ መሥራት ይኖርበታል ብለዋል።