በአፋር የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ከ17ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት ኬሚካል ተረጨ - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ከ17ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት ኬሚካል ተረጨ
ሰመራ ጥቅምት 14/ 2012 አፋር ክልል የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ከ17ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት ኬሚካል መረጨቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። በሚኒስቴሩ የተባይ ነፍሳት መከላከል ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ጋሻውጠና አስማማው ለኢዜአ እንዳስታወቁት ርጭቱ የተከናወነው በአውሮፕላን በመታገዝ ጭምር ነው። በክልሉ ከሰኔ 2012 ጀምሮ የተከሰተውን አንበጣ መንጋ ለመከላከል ኬሚካሉ በአውሮፕላን ከ3ሺህ 800 ሄክታር በላይ መሬት ላይ መረጨቱን አመልክተዋል። እንዲሁም መንጋው ጉዳት ያደርስባቸዋል በተባሉ ስምንት ወረዳዎች 14ሺህ ሄክታር በሚሆን መሬት ላይ የሰው ኃይል በማስተባበር ርጭቱ መካሄዱን አስረድተዋል። ርጭቱ መንጋው ሊያደርስ ከሚችለው ጉዳት አንጻር ውጤታማ ሊባል የሚችል ነው ያሉት ከፍተኛ ባለሙያው፣ ኅብረተሰቡ የአንበጣ መንጋውን እንቅስቃሴ በመጠቆምና ኬሚካል በተረጨባቸው አካባቢዎች ከእንስሳትና ሰው ንክኪ ነጻ በማድረግ መተባበሩን ተናግረዋል። በክልሉ ሌሎች 16 ወረዳዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በራስ አቅም ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። የአፋር ክልል እንስሳት፤ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ የእጽዋት ጤና ጥበቃ ባለሙያ አቶ ዓሊ መሐመድ መንጋው ሕይወቱ ከእንስሳት እርባታ ጋር የተቆራኘው አርብቶ አደር እጽዋትና የመኖ ሳርን በማውደም ለድርቅ ተጋላጭ እንዳያደርገው ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ለዚህም አርብቶ አደሩና በየደረጃው ያለው አመራር መንጋውን ለማስወገድ በሚደረገው አንቅስቃሴ እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል። የአንበጣ መንጋ በሶማሌና በአፋር ክልሎች ባለፈው ዓመት መከሰቱ ይታወሳል።