ቀጥታ፡

"ውህደቱ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው" - ምሁራን

ጥቅምት 14/2012 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባርና አጋሮቹ ውህደት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ምሁራን ገለፁ።

የአራት የፖለቲካ ድርጅቶች ጥምረት የሆነው ገዢው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) እና አጋር ፓርቲዎቹ ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲ የመቀየሩ ውጥን መነሳት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

ይህ ጉዳይ በየሁለት ዓመቱ በሚካሄደው የኢህአዴግ ጉባኤ ወቅት በየጊዜው ሲነሳ ቆይቷል፡፡ ባለፈው 2011 መስከረም ወር በአዋሳ በተካሄደው የድርጅቱ ጉባኤም ውሳኔው በይደር ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ኢህአዴግና አጋሮቹ ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲነት በቅርቡ እንደሚቀየሩ ማስታወቃቸው ይታወቃል።

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የውህደቱ እንድምታ ምን ይሆን ሲል ከምሁራን ጋር ቆይታ አድርጓል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪው አቶ ዮናስ ዘውዴ እንደገለፁት የውህደቱ ሀሳብ የዘገየ መሆኑን ገልፀዋል።

አቶ ዮናስ እንዳሉት ከአራቱ የግንባሩ ድርጅቶች ውጪ ያሉ የሶማሌ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ሀረሪ ክልል ገዢ ፓርቲዎች የተሻለ አቅም ቢኖራቸውም አገር የመምራት እድል አያገኙም።

በመሆኑም እነዚህ አጋር ድርጅቶች በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ በርካታ ህዝብ እየመሩ ኢትዮጵያዊ ሆነው የመሪነት እድል የተነፈጉ በመሆናቸው ውህደቱ ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን ይገልጻሉ።

የፓርቲው ውህደት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት እና ከማንነት ፖለቲካ ይልቅ ወደ ርዕዮት ፖለቲካ የሚያሸጋግር መሆኑንም በአስተያየታቸው አክለዋል።

በኢህአዴግ ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል ጥናትና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ተመስገን ብርቃ ውህደቱ ከኢህአዴግ ሰባተኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ጀምሮ ሲነሳ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በ2009 ዓም የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምሁራን ስብስብ በውስጥ ያለውን ችግር በሳይንሳዊ መንገድ ማስጠናት መፈለጉን በማውሳት ባለ 45 ገፁ የጥናቱ ውጤትም ውህደቱ የመፍትሄ ምክረ-ሀሳብ ሆኖ መምጣቱን ተናግረዋል።

ጥናቱ የተጠናቀቀ ቢሆንም በስራ አስፈፃሚ አባላትና በምክር ቤቱ ውይይት ያልተደረገበት በመሆኑ በ11ኛው የድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ጥናቱ ሊቀርብ አለመቻሉን ገልፀዋል።

በጥናቱ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እየተደረገ መሆኑን ገልፀው ውይይቱ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የኢህአዴግና የአጋሮቹ ውህደት ድርጅታዊ መስመር መሳቱን እና ከሚመራበት የማዕከላዊ ዴሞክራሲያዊነት መርህ ያፈነገጠ እንዲሁም ፌዴራሊዝምን የሚንድ አሃዳዊነትን የሚያንፀባርቅ ነው ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ መሰረተ ቢስ እና ጥናቱን ያላገናዘበ ነው ሲሉም አስረድተዋል።

ፓርቲን እና መንግስትን አንድ አድርጎ የማሰብ እሳቤ ደግሞ ውህደቱን በትክክል ካለ መረዳት የመነጨ ስሜት መሆኑን ይገልፃሉ።

ውህደቱ የዘገየ ነው የሚሉት ዶክተር ተመስገን የኢትዮጵያ ህዝብ ኢህአዴግ ከተመሰረተበት ዘመን አሁን ያለው መልክ የተቀየረ በመሆኑ ድርጅቱም የህዝቡን ለውጥ ተቀብሎ አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር ራሱን መቀየር አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም