ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሰው ኃይል ልማትና በሳይንስ ጥናት ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር መስራት ትሻለች

ጥቅምት 14 ቀን 2012 ኢትዮጵያ በሰው ኃይል ልማትና በሳይንስ ጥናት መስኮች ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር መስራት እንደምትፈልግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይና የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርትን ጨምሮ 10 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከአሜሪካ  ዩኒቨርሲቲዎች ጋር መስራት በሚፈልጉባቸው ጉዳዮች ላይ ዛሬ በአዲስ አበባ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ኦሃዮ ስቴት፣ ኦክላሃማ፣ ኢንዲያና፣ ቴክሳስ ቴክ እና ሌሎችም የአሜሪካ ዪኒቨርሲቲዎች ተሳትፈዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በምርምር ዘርፎች ውስንነት አለባት።

በተለይም የምርምርና የቴክኖሎጂ ስራዎች እየተሻሻሉ ቢመጡም ፈጣን እድገት እንደምታስመዘግብ አገር 'ከዚህ በላይ መጓዝ ይኖርባታል' ብለዋል።

ኢትዮጵያና አሜሪካ በትምህርት መስክ በመምህራን አቅም ማጎልበት የቆየ ትብብር እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ የትምህርት እድል አግኝተው የሚማሩ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውንና አገራቱ በአካዳሚክ ጉዳዮች በጋራ እየሰሩ እንደሆነም አክለዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የቆየ የትምህርት፣ የሳይንስና፣ የቴክኖሎጂ ትብብር ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ለምትተገብረው የትምህርት ፍኖተ ካርታ አጋዥ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ቅድሚያ በምትሰጣቸው በሳይንስ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በቴክኖሎጂና፣ በምርምር ዘርፎች በጋራ መስራት እንደምትፈልግም ነው የገለጹት።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱም የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር 'በትብብር የሚሰሩባቸው ጉዳዩች አሉ' ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያለባትን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እጥረት፣ ውስን የሴት ተመራማሪዎች ተሳትፎና ደካማ የምርምር ጥምረት ለማሻሻል 'ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ትሰራለች' ነው ያሉት።

አገሪቷን 'የአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ በምናደርገው እንቅስቃሴ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ልምድና ተሞክሮ አስፈላጊ ነው' ሲሉም አክለዋል።

በአሜሪካ ኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የግሎባል ዋን ሄልዝ ኢንሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር የወንድወሰን ገብረየስ 'በግብርናና ጤና ዘርፎች በጋራ እንሰራለን' ብለዋል።

ጅግጅጋና ጅማ ከቴክሳስ ቴክ፤ አዲስ አበባ፣ ሃሮማያና ሃዋሳ ከኦክላሃማ፤ ባህር ዳር ከኢንዲያና እንዲሁም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ 60 በመቶ ወጣትና ንቁ የሰው ኃይል፣ ከ40 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ያላት  መሆኗን በመጠቆም።

በመሆኑም ይህ እምቅ ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ ቀድሞ የነበረው ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም