ቀጥታ፡

ከኮምቦልቻ ባህር ዳር ቀጥታ በረራ ሊጀመር ነው --- የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ደሴ (ኢዜአ) ጥቅምት 14 ቀን 2012 ዓ.ም ---ከአንድ ዓመት በፊት ተቋርጦ የቆየው ከኮምቦልቻ ባህር ዳር የቀጥታ በረራ ሊጀመር መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ። በረራው ከጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚጀመር ተመልክቷል። በአየር መንገዱ የደሴ-ኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ቃለአብ ለኢዜአ እንደገለጹት ከኮምቦልቻ ባህር ዳር በሳምንት አንድ ቀን ሲደረግ የነበረው የቀጥታ በረራ የመንገደኞች ቁጥር በሚፈለገው መልኩ ባለመኖሩ ከአንድ ዓመት በፊት ተቋርጧል። በተለያዩ ጊዜያት የሚንጠባጠቡ መንገደኞችን በአዲስ አበባ በኩል ወደ ባህር ዳር በቅብብሎሽ እንዲጓጓዙ ሲደረግ መቆየቱንም አስታውሰዋል። “በአሁኑ ወቅት በኮምቦልቻ ከተማ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ፍሰት እየጨመረ በመምጣቱና ከህብረተሰቡ እየተነሱ ያሉ የፍላጎት ጥያቄዎች በመጨመራቸው በረራውን ዳግም ማስጀመር አስፈልጓል” ብለዋል ። “ከጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የቀጥታ በረራው ይጀመራል” ያሉት ኃላፊው በረራውም ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ረቡና ቅዳሜ ባሉት ቀናት በሳምንት ለአራት ጊዜ እንደሚካሄድ አመላክተዋል ። ከኮምቦልቻ በአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር በሚደረግ በረራ በፍተሻና ተራ በመጠበቅ ከሦስት ሰዓት በላይ እንደሚፈጅ የገለፁት ኃላፊው የቀጥታ በረራው 40 ደቂቃ ብቻ የሚፈጅ በመሆኑ ለመንገደኞች ጊዜ፣ እንግልትና ወጭን እንደሚቀንስ አስረድተዋል። የደሴ ከተማ ነዋሪ አቶ አህመድ መሐመድ በሰጡት አስተያየት ለተለያዩ የግል ሥራዎች ወደ ባህር ዳር በተደጋጋሚ እንደሚመላለሱ ተናግራዋል፡፡ ከኮምቦልቻ፣ በአዲስ አበባ፣ ባህርዳር በቅብብሎሽ የሚያደርጉት የአየር ጉዞ ተጨማሪ ክፍያና እንግልት እንዳለው የገለፁት አቶ አህመድ የቀጥታ በረራ መጀመሩ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም