ከጩኮ ሀገረማርያም አገር አቋራጭ አስፋልት መንገድ የዲዛይንና የጥራት ችግሮች አሉበት - ኢዜአ አማርኛ
ከጩኮ ሀገረማርያም አገር አቋራጭ አስፋልት መንገድ የዲዛይንና የጥራት ችግሮች አሉበት
ዲላ ጥቅምት 14/ 2012 ከጩኮ ሀገረማርያም በመገንባት ላይ ያለው አገር አቋራጭ አስፋልት መንገድ የዲዛይንና የጥራት ችግሮች ለጉዳት እንዳደረጋቸው ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋረዎቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት ሁለቱን ከተሞች ለማገናኘት እየተገነባ ያለው መንገድ ባሉበት ችግሮች ጉዳት እየደረሰባቸው ነው። የገደብ ወረዳ ነዋሪ አቶ አየለ ዱማሮ በገደብ ከተማ የተሰራው አስፋልት መንገድ የጎርፍ መውረጃው ከመንገድ በታች ባሉ ነዋሪዎች በማፍሰስ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል። በከተማው ዝናብ በሚጥልበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ ጎርፉ ቤት ሰብሮ በመግባት ንብረት ማውደሙ ሳያንስ፤ይዞት በሚመጣው ቆሻሻ ለበሽታ እየተጋለጡ መሆናቸውን ገልጸዋል። በይርጋ ጨፌ ወረዳ የዶማረሶ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ኤልያስ ቁጦ አካባቢው ተራራማ የመገዱን ዳገትነት ለመቀነስ የተቆረጠው ኮረብታና ተራራ ናዳ በማስከተል ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል። ችግሩ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል። የዳራ ወረዳ ነዋሪው አቶ ንጉሴ ጥላሁን አስፋልቱ ተሰርቶ ግንባታው በተጠናቀቀ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፈራረሱንና የከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ክብደት መሸከም አቅቶት እየሰመጠ ነው ብለዋል። የጌዴኦ ዞን መንገድና ትራንስፖርት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉነህ ዋቆ በበኩላቸው መንገዱ ዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያለው መንገድ ቢሆንም፤ የጥራትና የዲዛይን ችግሮች እንዳሉበት አምነዋል። የጎርፍ መውረጃ ቦዮችንና መጋቢ መንገዶች ከዋናው መንገድ ጋር አስተሳስሮ ከመሰራት አንጻር ችግሮች እንደሚታዩበት አስታውቀዋል። በተለይም የዞኑ የመሬት አቀማመጥ ተራራማና ኮረብታማ መሆንም ችግሩን እንዳባባሱት መሆኑን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የደቡብ ሪጅን ዳይሬክተር ኢንጂነር ደጀኔ ጉቱ በበኩላቸው መንገዱ በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። መንገዱ በደረጃው መሠረት ወጥ በሆነ ዲዛይን ወደ ግንባታ የተገባ ቢሆንም፤ የከተሞችን እድገት የሚመጥን የዲዛይን ከለሳ እየተደረገነው ብለዋል። ይሁንና መሠረታዊ የሆነ የዲዛይንና የጥራት ችግሮች ያሉባቸው አከባቢዎች ተለይተው እንደሚስተካከሉ አመልክተው፣የሥነ ምህዳር ምቹ አለመሆን የፕሮጀክቱ ፈተና ሆኗል ብለዋል። ከጥራት መጓደል ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ያስረዱት አንጄኒዬር ደጀኔ፣ መንገዱ በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚደረግም አስረድተዋል። ፕሮጀክቶ ከሀዋሳ ሀገረማርያም 200 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ የተጀመረው በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር።