ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን ሁከት የማረጋጋት ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል - የመከላከያ ሚኒስቴር

ኢዜአ፤ ጥቅምት 14/ 2012 በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስተው በነበሩ ግጭቶች የተዘጉ መንገዶችና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን የማስከፈት ስራ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከአባገዳዎች፣ ከወጣቶችና ከክልሉ የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን እየሠራ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስቴር ገለጸ። 
ሚኒስቴሩ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ሠላም ወዳዱ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ፣ ወጣቶች፣ አባ ገዳዎችና የክልሉ የጸጥታ አካላት ሁከቱ እንዳይባባስ ያደረጉትን አስተዋፅኦ አድንቋል። የመከላከያ ሚኒስቴር ሰሞኑን በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ተከስተው የነበሩ ሁከቶችን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። በሚኒስቴሩ የኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ሰሞኑን የፀጥታ መደፍረስ በተከሰተባቸው በኦሮሚያ ሀረርና ድሬዳዋ አካባቢዎች ሠራዊቱ ከአባ ገዳዎች፣ ከሃይማኖት መሪዎችና ከአካባቢው ወጣቶች ጋር በመሆን የማረጋጋት ስራ እያከናወነ ነው። የክልሉ መንግሥት ለፌዴራሉ መንግስት ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ሠራዊቱ የፀጥታ ችግር በተከሰተባቸው በተለይም በአምቦ፣ ቢሾፍቱ፣ ባሌ ሮቤ፣ አዳማ፣ ሞጆ፣ ድሬዳዋና ሀረር መሰማራቱን ገልጸዋል። በእነዚህ አካባቢዎች የተዘጉ መንገዶችን የማስከፈትና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ሥራ የማስጀመር እንቅስቃሴ መከናወኑንም ሜጄር ጄኔራል መሀመድ ተናግረዋል። አካባቢውን በማረጋጋቱ ሂደት የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሠላም ወዳዱ ሕዝብ ላደረገው አስረዋፅኦ መከላከያ ሚኒስቴር ምስጋና አቅርቧል። ሠራዊቱ ከኅብረተሰቡ ጋር በሠራው ሥራ ተጨማሪ የሰው ህይወትና ንብረት ከጥፋት ማትረፍ እንደተቻለ ያስረዱት ሜጀር ጄኔራሉ ሠራዊቱ ባልደረሰባቸው አካባቢዎች በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል። 'ሠላምን በታጠቀ ኃይል ብቻ ማረጋጋት አይቻልም' ያሉት ሜጀር ጄኔራል መሀመድ ሠላም ለማስፈን የህብረተሰቡ ሚና ከፍ ያለ መሆኑን ገልፀዋል። በመሆኑም ኅብረተሰቡ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንድቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። የፀጥታ መደፍረስ ባጋጠመባቸው አካባቢዎች የሚገኘው ሠራዊት አካባቢዎቹ ወደ ቀደመ ሠላማቸው እስከሚመለሱ የአገር መከላከያ ሠራዊት አካባቢዎቹን የማረጋጋቱን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ሁከት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሠላም እንዲመለስ አስተዋፅኦ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ሁሉ የሠራዊቱን ሕዝባዊ ወገናዊነት በሚሸረሽር መልኩ መልዕክት ያስተላለፉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አስታውቀዋል። ትናንት በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተከሰተውን ሁከት አስመልክተው መግለጫ መስጠታቸው ይታወቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም