ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከተለያዩ አገራት ጋር በስምምነት እየሰራች ነው - ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ኢዜአ ጥቅምት 14 / 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከተለያዩ አገራት ጋር በስምምነት እየሰራች መሆኗን ኢትዮጵያ የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከተለያዩ አገራት ጋር በስምምነት እየሰራች ነው - ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርገለጸ። ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ያለመና 'የሰማያዊ ልብ' ዘመቻ የሚል ዓለም አቀፍ መርሃ ግብር ትናንት ማምሻውን በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል። ''እኔም በልቤ ቃል እገባለሁ'' በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው በዚህ መርሃ ግብር ላይ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ኃላፊዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳትፈዋል። ከአዲስ አበባ ካሉት ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ሴቶችና ወጣቶችም እንዲሁ መርሃ ግብሩን ታድመዋል። መርሃ ግብሩ በሰዎች የመነገድ ወንጀል ተጠቂ ለሆኑ ሰዎች ርህራሄን ማሳየት፣ መደገፍና ወንጀሉን ለመከላከል ሁሉም የበኩሉን ለመወጣት ቃል የሚገባበት ነውም ተብሏል። ሰማያዊ ልብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻው ከኢትዮጵያ ውጭ በ12 አገራት የተካሄደ ሲሆን በኢትዮጵያ ትናንት ማምሻውን የተከናወነው መርሃ ግብር በምስራቅ አፍሪካ ሲካሄድ ይኸ የመጀመሪያው ነው። ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ጥናት እንደሚያመለክተው በመካከላኛው ምስራቅ አገራት ከሚገኙት ኢትዮጵያውያን መካከል 76 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆኑት የሕገ ወጥ ዝውውር ሰለባዎች ናቸው። በተለይም እንድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑት ወደ ተለያዩ ሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ለስራ ፍለጋ እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች ከተጓዙት ኢትዮጵያውያን መካከል 7 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ13 እስከ 17 ሲሆኑ ከዚሁ ውስጥ 87 ነጥብ 1 በመቶ በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ለኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እንደሚዳረጉም ነው ጥናቱ የሚጠቁመው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተወካይ አምባሳደር ማህሌት ኃይሉ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በመታገዝና ለዜጎች ቅድሚያ በመስጠት እየሰራች ትገኛለች። ''አገራችን ይህንን በሰዎች የመነገድ ወንጀልን ለመቀነስ ከተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋርም በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ስራዎች ስምምነት በመፈረም፣ በትብብር በመስራትና የጋራ ስራዎች መሬት እንዲነኩ የበኩሏን ጥረት በማድረግ ላይም ነች'' ነው ያሉት። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተደራጁ ወንጀሎችና አደንዛዥ ዕጽ ቢሮ የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ዶክተር አማዶ ፊሊፕ በበኩላቸው ዓለም አቀፍ የሰማያዊ ልብ ዘመቻ በሰዎች የመነገድ ወንጀልን አስቀድሞ መከላከልና ተጎጂዎችን በመንከባከብ መርህ ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል። እንደዚህ ዓይነት ዘመቻዎች አገራት በፖለሲና ስትራቴጂዎቻቸው አካታው በትኩረት እንዲሰሩ የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት ዶክተር አማዶ፤ በተለይ ሴቶችና ወጣት የሲቪል አደረጃጀቶችን በማሳተፍ የግንዛቤ ማሰፋት ስራውን የሚያጠናክርም ነው ሲሉ ገልጸዋል። የሚመከለታቸው የመንግሥት አካላትም በዝውውሩ ላይ የሚሳተፉ ወንጀለኞችን ለሕግ በማቅረቡ ላይም በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበው ድርጅቱ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ወንጀሉን ለመካላከል የኢትዮጵያ መንግሥት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል። ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እንደተናገሩትም፤ መንግሥት በወንጀሉ ላይ የሚሳተፉ ሰዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ጎን ለጎን በጠቅላይ አቃቤ ሕጉ የሚመራ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ግብረ ኃይል ተደራጅቷል። ግብረ ኃይሉ ወንጀልን መከላከል፣ አጥፊዎች ተገቢው ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ፣ ከስደት ተመላሽ ዜጎችን መልሶ ማቋቋምና ጥናትና ምርምር በማካሄድ መፍትሄ የማፍለቅ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።                              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም