በትግራይ የሚገኙ የጣልያን ወታደሮች መቃብሮችን ለቱሪዝም አገልግሎት እንዲውሉ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ የሚገኙ የጣልያን ወታደሮች መቃብሮችን ለቱሪዝም አገልግሎት እንዲውሉ ተጠየቀ
መቐለ ጥቅምት 14 / 2012 በትግራይ ክልል የሚገኙ የጣልያን ወታደሮች መቃብሮችን ለቱሪዝም አገልግሎት ለማዋል ትኩረት እንዲሰጥ ወጣቶችና የቱሪዝም ባለሙያዎች ተናገሩ። የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መቃብሮቹን የቱሪስት መዳረሻና የገቢ ማስገኛ ለማድረግ እየሰራ ነው ይላል። ኢትዮጵያን በጣልያን የወረረችባቸውን ጦርነቶች ተከትሎ መቃብሮቹ በአድዋ፣አዲግራት፣በመቀሌና በማይጨውና በቆላ ተምቤን ወረዳ ወርሰገ በተባለ ልዩ ሥፍራ ይገኛሉ። መቃብሮቹ ከለላና ጥበቃ እየተደረገላቸው ቢሆንም፤ ለጎብኚዎች እንዳልተዋወቁ አስተያየት ሰጪዎቹ ይገልጻሉ። ከአስተያየት ሰጪዎቹ በማዕከላዊ ዞን የቆላ ተምቤን ወረዳ ነዋሪ ወጣት ገብረአምላክ አብርሃ ወርሰገ በተባለ ቀበሌ ገበሬ ከ10ሺህ 800 የሚበልጡ ጣልያናውያን ወታደሮች መቃብር እንደሚገኝ ገልጿል። ሥፍራው ኢትዮጵያውያን ታሪክ ሰሪነታችን ነጋሪ ከመሆኑ ባሻገር፤ ለቱሪስት መስህብነት በማዋል ገቢ ሊገኝበት ይገባል ብለዋል። አስተዳደሩ የመሠረተ ልማት ተቋማትና ማረፊያ መስራት እንደሚጠበቅበት ተናግሯል። ''በቱሪዝም ልማት ተሰማርተን ታሪካችን ከማስተዋወቅ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችን ለማረጋገጥ የጣልያን ወታደሮች መቃብሮችን ለቱሪዝም መስህብ አገልግሎት መዋል ይገባቸው ነበር'' ያለችው ደግሞ የአድዋ ከተማ ነዋሪዋ ወጣት መብራት ትኩእ ናት። በመቐለ እንዳየሱስ ተራራ ላይ የሚገኝ ከ500 በላይ የጣልያን ወታደር መቃብሮች እንደሚገኙም የተናገሩት የቱሪዝም ልማት ባለሙያ አቶ ጎይተኦም አድማሱ ናቸው። መቃብሮቹን አንዴ ''የሚያስተዳድረው የጣልያን ኤምባሲ ነው ''እየተባለ፣ሌላ ጊዜ ደግሞ በበጀትና በሰው ኃይል እየተመካኘ ሳንጠቀምባቸው ቀርተናል ብለዋል። ''በእጃችን ያለን ሃብት ባለመጠቀማችን ሊቆጨን ይገባል።ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ ይኖርብናል'' ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ዘነቡ ሀለፎም በበኩላቸው ለቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት አናሳ ስለነበር መቃብሮቹ የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን በማስጎብኘት ገቢ ለማመንጨት ሳይቻል መቆየቱን አምነዋል። በዚህ ዓመት መቃብሮቹን በማስተዋወቅና በጀትና ባለሙያዎች በመመደብ ሥራ ለመፍጠርና ገቢ ለማመንጨት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገልጸዋል። ትግራይ በ1888ና በ1928 ከጣልያን ጋር የተካሄዱ ጦርነቶች ማስተናገዷ ይታወሳል። የትግራይ ክልል የበርካታ ተፈጥሯዊ፣ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት ነው።