የእምነት አባቶች ተከታዮቻቸውን በማስተማር ለሀገር ሰላም እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የእምነት አባቶች ተከታዮቻቸውን በማስተማር ለሀገር ሰላም እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ
ሀዋሳ ቅምት 13/2012፡- የእምነት አባቶች ተከታዮቻቸውን በማስተማርና በመምከር ለሀገር ሰላም እንዲሰሩ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቀረበ። ከትናንት ጀምሮ በኦሮሚያ አንዳንድ ከተሞች ሁከት በመቀስቀስ የማይመለከታቸው አካላትና የእምነት ተቋማት የፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ ለማድረግ የተካሄደው እንቅስቀሴ ተገቢነት እንደሌለው ተመልክቷል። የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ዛሬ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት ከግጭት ተጠቃሚ የሚሆን ማንም እንደሌለ በመረዳት በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት ለማስቆም ሊሰራ ይገባል። ግለሰቦችና ቡድኖች በለኮሱት እሳት የብዙሀን ህይወት እንዲጠፋና በእምነት ልዩነት እየፈጠሩ በእርስ በማጋጨት ሀገሪቱ የጦርነት አውድማ እንድትሆን የሚፈልጉ እንደሉ ተናግረዋል። ይህንን በተረጋጋና በሰከነ ሁኔታ ግጭቱ እንዳይሰፋ ሁሉም አካላት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል። “ትናንት በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ከተሞች ውስጥ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸው የእምነት ተቋማት ላይ ለማቃጠል ሲሞከር እንደነበረ ተመልከተናል “ ብለዋል። “ጥያቄው ሌላ ተጎጂ የሚሆነው አካልና ተቋም ሌላ እየሆነ ነው “ ያሉት ጠቅላይ ጸሐፊው የኃይማኖት አባቶችና መሪዎች ተከታዮቻቸው በማስተማር ለሀገር ሰላም እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ድርድር የሌለው ህግን የማስከበር ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አመልክተው የሰላም ስጋትና ጥፋት የሆኑ አካሄዶችን ከአሁን በኋላ መታገሱ ሊበቃው እንደሚገባም ጠቁመዋል። መንገድ እየተዘጋ ሰዎች በህገመንግስት የተሰጣቸው ከቦታ ወደ ቦታ የመዘዋወር መብት በህገወጦች እየተገደበ በመሆኑ ስርዓት ማሲያዝ ይገባል። ከዚህ በኋላ የእምነት ተቋማትን ለማቃጠል መነሳትና ማነሳሳት ዋጋ እንደሚያስከፍል የገለጹት ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ የየትኛውም የእምነት ተቋማት ለጥቃት እንዳይጋለጥ ከለላና ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አመልክተዋል። “ የእምነት ተቋማት የመጸለያ ቦታ ናቸው ፤የፖለቲካ ማራመጃ አይደሉም” ብለዋል።