የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር  ማብራሪያና የዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች

92
ሰኔ 12/2010 የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ትናንት ከሰዓት ለህዝብ ተወካዮቸ ምክር ቤት አባላት አጭር ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ በወቅታዊ ሀገራዊ  ጉዳዮች ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎችም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ዓለም ዓቀፍ መገነኛ ብዙኃን የጠቅላይ ሚኒትሩን ሪፖርትና ማብራሪዎችን የተመለከቱ ዘገባዎችን ይዘው ወጥተዋል፡፡ የቻይናው የዜና ወኪል ዥንዋ  የኢትዮጵያ መንግሥት ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከር እየወሰዳቸው  ያሉ እርምጃዎች የህዝቦችን አንድነት ማጠናከሩንና የሀገሪቱን ደህንነትም ማረጋገጡን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ ጠቅሶ አስነብቧል፡፡ ብሔራዊ መግባባትን ለማጠናከር ከተሰሩ የተለያዩ ስራዎች በተጨማሪ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የተደረጉ ውይይቶችም  የሀገሪቱን ደህንነት ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገራቸውንም ነው ዘገባው  ያመለከተው፡፡ ባለፉት ጊዜያት በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የነበረው አለመረጋጋት ሀገሪቱን ሁለት ጊዜ የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ እንድታውጅ ያስገደዳት ሲሆን  ይህም ትልቅ ተጽእኖ አሳድሮ መቆየቱን ዘገባው አመላክቷል፡፡ በቅርቡ የተካሔደውን የስልጣን ሽግግር ተከትሎ የተወሰዱ እርምጃዎች የነበረውን አለመግባባት ማርገባቸውንና አሉታዊ አመለካከቶችን መቅረፋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡ የቱርኩ የዜና ምንጭ አናዳሎ ደግሞ ጠቅላይ ሚነስትሩ የሀገሪቱን የእዳ ጫና በተመለከተ የሰጡትን ማብራሪያ ይዞ ወጥቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ባቀረቡት አመታዊ ሪፖርት የሀገሪቱ የብድር ጫና  ለኢኮኖሚው ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን አብራርተዋል፡፡ ሀገሪቱ በመጀመሪያው ግማሽ በጀት ዓመት ብቻ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር የተበደረች ሲሆን ይህም የሀገሪቱን ጠቅላላ የብድር መጠን ወደ 24 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንዳሳደገውም በሪፖርታቸው ማብራራታቸውን ዘገባው አትቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ የወጪ ንግዱ እንድገት 0 ነጥብ 02 በመቶ እንደነበርና የንግድ ሚዛኑ ደግሞ በ2 ነጥብ 2 በመቶ መስፋቱ ኢትዮጵያን ለውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደዳረጋትም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ያብራሩት፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሪፖርትና ማብራሪያ ካስነበቡ ዓለም ዓቀፍ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች መካከል ቢቢሲ በተለይ ከሽብር ጋር በተያያዘ ለእስራት ተዳርገው የነበሩ እስረኞችን መለቀቅ አስመልክቶ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት  የተነሳውን ጥያቄና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ ይዞ ወጥቷ፡፡ በዚህም  “ማንም ይሁን ማን ህገመንግሥቱን ማክበር” እንዳለበትና ከእስረኞች አያያዝ ጋር በተያያዘ በመንግስት በኩልም ችግሮች እንደነበሩ የሰጡትን ማብራሪያ በድረገጹ አስነብቧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው ከኤርትራ ጋር ያለውን የድንበር ግጭት ለማስቆም ያሳለፈው ውሳኔ  የሁለቱንም ሀገራት ፍላጎት መሰረት ያደረገ መሆኑንም ቢቢሲ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ በመንግስት የዞታ ስር በነበሩ ኩባንያዎች የግሉ ዝርፍ የአክስዮን ድርሻ እንዲኖረው የተላለፈው ውሳኔ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማዘመን የጎላ እስተዋጽኦ ይኖረዋል በሚል ያነሱትን ሃሳብም በዘገባው አካቷል፡፡ ሲ ኤን ኤን ደግሞ በቴሌኮም ዘርፉ ሊደረግ የታሰበው ሪፎርም ተወዳዳሪነቱን ያሳድገዋል በሚል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትን ማብራሪያ ይዞ ወጥቷል፡፡ ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ 12 ሚሊዮን ህዝብ ባላት ሶማሊያ 4 የቴሌኮምዩኒኬሽን ኩባንያዎች እንዳሏት ጠቅሰው 100 ሚሊዮን ህዝብ ባላት ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የቴሌኮም ኩባንያ ብቻውን ተወዳዳሪ እንደማይሆን አስመልክተው የሰጡትን ማብራሪያ በማሳያነት ጠቅሷል፡፡ የአክስዮን ድርሻው ለሽያጭ ከመብቃቱ በፊትም በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ጥናትና ውይይት እንደሚደረግበት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ ጠቅሶ ሲ ኤን ኤን ዘግቧል፡፡ የውጭ ኩባንያዎችም የውሳኔውን አፈጻጸም እየተጠባበቁ መሆናቸውን ያመለከተው ዘገባው ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በተያዘው ወር  ኤምቲኤንና ቮዳኮም የተሰኙ የቴሌኮም ኩባንያዎች በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን  አስታውሷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም