የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር በከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች ግድያ ተጠርጥረው የተያዙ እስረኞችን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር በከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች ግድያ ተጠርጥረው የተያዙ እስረኞችን ጎበኙ
አዲስ አበባ ጥቅምት 13/2012 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በሰኔ 15ቱ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች ግድያ ተጠርጥረው ቁጥጥር ስር የሚገኙ እስረኞችን ጎበኙ። ተጠርጣሪዎቹ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በባህር ዳር እና አዲስ አበባ በተፈጸመው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ግድያ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል። በዚሁ ወንጀል ተጠርጥረው በአዲስ አበባ የሚገኙ እስረኞች ያሉበትን ሁኔታ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ጎብኝተዋል። "በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ በሕግ የሚፈቀደው የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ በአብዛኛው የተጠናቀቀ በመሆኑ ከዚህ በላይ ሊቆዩ አይገባም" ብለዋል ኮሚሽነሩ። ተጠርጣሪዎቹ ከ 3 እስከ 4 ወራት ያክል የፖሊስ ምርመራን ለማጠናቀቅ በሚል በእስር የቆዩ መሆናቸውንም አስታውሰዋል። በጉብኝታቸው ሴቶች የታሰሩበት ክፍል በአንፃራዊነት የተሻለና የጽዳት ደረጃው የተጠበቀ መሆኑን ተመልክተዋል። በየእለቱ ከቤተሰብ፣ ወዳጅ እና የሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘት መቻላቸውንም በበጎ ጎኑ አንስተዋል።