የመንግሥታቱ ድርጅት ለዓለም ሠላምና ደህንነት መስራቱን ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሥታቱ ድርጅት ለዓለም ሠላምና ደህንነት መስራቱን ይቀጥላል
ጥቅምት 13/2012 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወደ ፊትም የዓለምን ሠላምና ደህንነት በማስጠበቅ ለስርዓተ ጾታ እኩልነትም እንደሚተጋ አስታወቀ። የድርጅቱ 74ኛ የምስረታ በዓል በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ የተለያዩ አካላት በተገኙበት ተከብሯል። በበዓሉ ላይ የታደሙት የመንግስታቱ ድርጅት ምክትል ዋና ፀሃፊ አሚና መሀመድ የድርጅቱን ዋና ፀሃፊ መልዕክት ያቀረቡ ሲሆን 'ድርጅቱ በርካታ ጉዳዮችን እየከወነ ለዚህ በቅቷል' ብለዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ የመንግሥታቱ ድርጅት ትኩረት የሚያደርገው የዓለም ሕዝቦች ዋና ዋና ችግሮች በሚላቸው ጉዳዮች ላይ ነው። የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል፣ ለሰብዓዊ መብት መጠበቅና ለስርዓተ ጾታ እኩልነት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል። ድርጅቱ በአስቻጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉትን ለመታደግ ሠላምን የማስጠበቅ ስራዎችን ከምንም በላይ እየሰራበት ይገኛል ብለዋል። ምክትል ዋና ጸሃፊዋ የመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል አካባቢን አረንጓዴ የማድረግ ዘመቻን በመቀላቀሉ አድንቀዋል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የወከሉት አምባሳደር ማህሌት ኃይሉ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እንደ መስራች አባልነቷ ከድርጅቱ ጋር ጥብቅ ግንኙነት አላት ብለዋል። ሆኖም በዚህ ወቅት ከአገራት እርስ በርስ ግጭቶች ጀምሮ የተደራጁ ወንጀሎች፣ ሽብርተኝነትና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ለዓለም ሠላም ፈተና ሆነዋል ነው ያሉት። ይህን ችግር ለመከለከል ጠንካራ የጋራ ጥረት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ኢትዮጵያም በዚህ ረገድ ጠንካራ ስራ እየሰራች ትገኛለች ሲሉ ተናግረዋል። በአፍሪካ ሕብረት የንግድና ኢንዱስትሪ ኮሚሽነር አልበርት ሙቻንጋም እንዲሁ የመንግስታቱ ድርጅት በዓለም ዙሪያ በርካታ የሠላም ግንባታ ስራዎችን ሰርቷል ይላሉ። ድርጅቱ በዓለም ዙሪያ ከትምህርትና ጤና አንስቶ በቅርቡ ደግሞ ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ አውሮጳዊያኑ አቆጣጠር ከ1945 ጀምሮ የዓለም አገራትን በአባልነት አቅፎ በዓለም ዓቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ሲሰራ ቆይቷል።