ማኅበሩ ለኢትዮጵያ ብልፅግና በአጋርነት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
ማኅበሩ ለኢትዮጵያ ብልፅግና በአጋርነት ይሰራል
ኢዜአ ጥቅምት 13/2012፡- ኢትዮጵያን ለማበልፀግ በመንግስት የተያዘውን ርዕይ ለመደገፍ በአጋርነት እንደሚሰራ ዜድ.ኤም የተሰኘ አክሲዮን ማኅበር አስታወቀ። አክሲዮን ማህበሩ እያከናወናቸው ባሉ ተግባራት ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የማህበሩ ቢዝነስ ዲቨሎፕመንትና ማርኬቲንግ አማካሪ አቶ የምወድህ ታደለ እንዳሉት ማህበሩ በ2010 ዓ.ም የተመሰረተና 210 ባለድርሻዎች ያሉት የጋራ ኢንቨስትመንት ነው። "የጋራ የብልፅግና መስመር ለትውልድ አጀንዳ” በሚል ቃልኪዳን የተመሰረተና ከአራት ዓመት በኃላ የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን ስም የሚያስጠራ አንድ ወይም ሁለት ምርት ለዓለም የማሳየት ዕቅድ ያለው ነውም ብለዋል። ማህበሩ በምዕራፍ አንድ በታዳሽ ኃይል ማመንጨት፣ በወተትና ወተት ተዋፅኦ፣ በእንቁላል ምርት አቅርቦትና ማቀነባበርና በዘመናዊ የከተሞች ትራንስፖርት አቅርቦት እስከ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚፈጁ ስራዎችን ለመከወንም አቅዷል። አቶ የምወድህ የስነ-አመለካከት ገቢረ-ስልጠና በመስጠት ረገድ እያከናወናቸው ያሉ እንዲሁም ሊያሳካቸው እየሰራባቸው ያሉ ተግባራትንም አብራርተዋል። ስልጠናው በፍጥነት ያደጉ አገራት እይታ፣ የአመራር ፍልስፍና፣ የስነ-ምግባር መርሆና መሰል ነገሮች የሚሰጡ ሲሆን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ስራ ፈጣሪዎች፣ ወጣቶችና ሠራተኞች ይሳተፉበታል። ለሰልጣኞቹ የስራ ዕድል የማመቻቸት ስራም ይከናወናል ብለዋል። እስከ ቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ለ150 ሺህ ሰዎች ስልጠናውን ለመስጠት ዝግጅት መደረጉንና ስልጠናው የሚሰጥበት ተቋምም በእነዚህ ዓመታት ለመገንባት መታቀዱን ገልጸዋል። ስልጠናውን የሚሰጡ ባለሙያዎች ከአገር ውስጥና ደቡብ ኮሪያ ከሚገኘው የማይንድ ኢጁኬሽን ሴንተር መዘጋጀቱም ተነግሯል። ይህ ስልጠና ከደቡብ ኮሪያ በመጡ አሰልጣኞች በሙከራ ደረጃ ለ500 ሰዎች መሰጠት መጀመሩም ተጠቅሷል። በቀጣዩ ዓመት በቀን 100 ሺህ ሊትር የሚያመርት የወተትና የወተት ተዋፅኦ ማቀነባበሪያ ለመክፈት እየተሰራ መሆኑንም ነው አቶ የምወድህ የገለፁት። በደቡብ ኮሪያ ከሚገኙ 9 ኩባንያዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙንና በአጋርነት ፋብሪካዎችን ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አንስተዋል። በጨርቃጨርቅ፣ በሪል ስቴት፣ በትራንስፖርት፣ በኮንስትራክሽንና መሰል ዘርፎች ከደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች ጋር ለመስራት መስማማታቸውንም ጠቅሰዋል። ከኢንቨስትመንት ጎን ለጎን ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት መታቀዱንና ፋብሪካዎች በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ክሊኒክና ትምህርት ቤቶች ለመስራት መታቀዱን ጠቅሰዋል። ማህበሩ መንግስት በያዘው የብልፅግናና የልማት ጎዳና ላይ በአጋርነት ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል። ማህበሩ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ባሉት ሁለት ዓመታት አባላት የማሰባሰብና ህጋዊ መደላድሎችን የመፍጠር ተግባር ሲከናወን መቆየቱንም አስረድተዋል። ዛየን ማውንቴን /ዜድ/ኤም/ አክሲዮን ማህበር በምዕራፍ አንድ ሊሰራቸው ካሰባቸው በተጨማሪ በምዕራፍ ሁለት የመኪና መገጣጠሚያ፣ የሪል ስቴትና ሌሎች ኢንቨስትመንቶችን ለመከወን አቅዷል ተብሏል።