ቀጥታ፡

በ150 ሚሊዮን ብር የተገነባው አዳሪ ትምህርት ቤት ስራ ጀመረ

ሆሳእና ፤ ጥቅምት 13/2012 በሀድያ ልማት ማህበር በ150 ሚሊዮን ብር የተገነባው የ”ሊች ጎጎ” አዳሪ ትምህርት ቤት 45 ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር መጀመሩን ልማት ማህበሩ ገለፀ፡፡

የሀድያ ልማት ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሞላ አቦ እንደገለፁት ልማት ማህበሩ በዞኑ በመንግስትና በህብረተሰቡ ያልተሸፈኑ የመሰረተ ልማቶችን በማሟላት ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው።

በ2008ዓ.ም ግንባታው ተጀምሮ ዘንድሮ የተጠናቀቀው አዳሪ ትምህርት ቤት ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው 45 ተማሪዎች ተቀብሎ ስራ እንዲጀምር መደረጉን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

አዳሪ ትምህርት ቤት ማስገንባት ያስፈለገበት ምክንያት በሰው ሀብት ልማት ላይ በማተኮር ብቁና ተወዳደሪ ዜጎችን በማፍራት በሀገሪቱ የተጀመረውን የለዉጥ ጉዞ ከግብ ለማድረስ ነው ብለዋል።

ትምህርት ቤቱ የተሟላ ቤተ መጽሀፍት፡የመማሪያ፡የማደሪያ ፡የመመገቢያና የንጽህና መጠበቂያ ህንፃዎችን ጨምሮ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን የማስተማሪያ ግብዓቶች ያሟላ መሆኑንም አቶ ሞላ ጠቁመዋል፡፡

ለመጀመሪያ ዙር አርባ አምስት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው አዳሪ ትምህርት ቤቱ አዲሱን የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሰረት በማድረግ ከ 7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን የሚከታተሉ በአመት በአማካይ ከ300 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተማር አቅም ያለው መሆኑን ከስራ አስኪያጁ ገልፃ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም