የሰሊጥ ግብይት ስርአትና የሽያጭ ጊዜ ገደብ እንዲሻሻል ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሰሊጥ ግብይት ስርአትና የሽያጭ ጊዜ ገደብ እንዲሻሻል ተጠየቀ
ሁመራ (ኢዜአ) ጥቅምት 13 / 2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት በሰሊጥ ምርት ላይ ያለውን የግብይት ስርአት እንዲያስተካከል በትግራይ ምዕራባዊ ዞን በሰሊጥ ማምረትና ግብይት ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት ጠየቁ፡፡ ድርጅቱ የሚከተለው አስገዳጅ የግብይት ስርአት ሰሊጥ አምራች አርሶ አደሮችና ባለሀብቶችን ለኪሰራ እየደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ሰሊጥ በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብት አቶ መንግስቱ ሓድጉ ለኢዜአ እንዳሉት የምርት ገበያ ድርጅት ዝቅተኛ ብሎ በ4ኛ እና በ5ኛ ደረጃ የሚያስቀምጠውን የሰሊጥ ምርት ተገደው እንዲሸጡ እየተደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የምርት ገበያ ድርጅቱ የሚከተለው የገበያ ስርአት አምራቹን ለኪሳራ እየዳረገ በመሆኑ እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡ አቶ መንግስቱ እንዳሉት አሁን ያለው የግብይት ስርአት ካልተስተካከለ አንድ ኩንታል ሰሊጥ ለማምረት የሚወጣው ወጪና የመሸጫው ዋጋ የሚጣጣም አይደለም፡፡ የሰሊጥ መሸጫ ጊዜ ገደብ አንድ ወር ብቻ መሆኑ ለኪሰራ እየደረጋቸው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በሰሊጥ ምርት ላይ የተሰማሩት አርሶ አደር ገዐይ ፈራሕ ናቸው፡፡ ባለፈው ሐምሌና ነሀሴ ወር የአንድ ኩንታል ሰሊጥ ዋጋ 6 ሺህ እንደነበር ያስታወሱት አርሶ አደሩ በተያዘው ጥቅምት ወር አጋማሽ ዋጋው ወደ 3ሺህ 500 ብር ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል፡፡ ሰሊጥ የሚሰበሰብበት ጊዜ መሆኑን ተከትሎ ለመሸጫ የአንድ ወር ጊዜ ብቻ መሰጠቱ ዋጋ በግማሽ ያህል እንዲቀንስ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ የመሸጫ ጊዜ ገደብ ወደሦስት ወርና ከእዚያ በላይ ከፍ ካለ የወጋ ልዩነት ሊያመጣ ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸውም አርሶ አደር ገዐይ ተናግረዋል። በሰሊጥ ምርት ደረጃ አሰጣጥ ላይ ችግር መኖሩን የገለጹት ደግሞ በሰሊጥ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ወርቁ ንጋቱ ናቸው፡፡ "የምርት ገበያ ድርጅት ባስቀመጠው የሰሊጥ ደረጃ ምርቱን ለመሸጥ ስለምንገደድ ለችግር ተዳርገናል" ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት የኮርፕሬት ኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ነፃነት ተስፋይ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው ለኢዜአ በሰጡት ምላሽ እንዳሉት ድርጅቱ የተቋቋመበት ዋናው ዓላማ የሃገሪቱን ምርት በጥራትና በብዛት ተረክቦ ለዓለም ገበያ ማስተዋወቅ ነው፡፡ ሰሊጥ አምራቾች ዋጋን አስመልክተው ጥያቄ ቢኖራቸውም የሚገበያዩ አካላት እንጂ ድርጅቱ ዋጋ ለመቀነስም ሆነ ለመጨር ስልጣን እንደሌለው አስታውቀዋል። አቶ ነጻነት እንዳሉት ከሰሊጥ ምርት ደረጃ አሰጣጥ ጋር ተያይዘው ይነሱ የነበሩ ችግሮች በአሁኑ ወቅት እየተቀረፉ መጥተዋል፡፡ ለእዚህም እስከ አምስተኛ ደረጃ የነበረውን የሰሊጥ ምርት በአሁኑ ወቅት አንድ ደረጃ በመጨመር እስከ ስድስት እንዲሆን መፈቀዱን ነው በማሳያነት የጠቀሱት፡፡ "ከእዚህ በፊት ዝቅተኛ ደረጃ ተብሎ አምራቹ በግዴታ እንዲሸጥ ይደረግበት የነበረው አሰራር በአሁኑ ወቀት ጥራቱን እንደገና እንዲያስተካክል ተፈቅዷል" ብለዋል፡፡ ከሰሊጥ ምርት መሸጫ ጊዜ ገደብ ጋር በተያያዘ የተነሳው ጥያቄ ለአሰራር አስቸጋሪ በመሆኑ በነበረው በአንድ ወር የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲቀጥል መደረጉንም አቶ ነጻነት አመልክተዋል፡፡ የሰሊጥ መጋዝኖች የማቆያ ሳይሆኑ የመቀበያ በመሆናቸው ምርት ፈጥኖ ካልተሸጠ በመጋዘኖቹ ሌላ አዲስ ምርት ለማስገባት እንደሚያስቸግር አስረድተዋል፡፡ ምርት ገበያ ድርጅት ምርቱን ለመቀበል ከሌሎች መስሪያቤቶች በጊዜያዊነት ያገኘውን መጋዝን ይጠቀም እንደነበር ያስታወሱት አቶ ነጻነት በአሁኑ ወቅት 150 ሺህ ኩንታል ሰሊጥ የመያዝ አቅም ያለው የራሱን መጋዝን በማስገንባት ላይ መሆኑን አስረድተዋል። ባለፈው ዓመት ድርጅቱ በሁመራና አካባቢው ከ600 ሺህ በላይ ኩንታል ሰሊጥ ያገበያየ ሲሆን ዘንድሮም ከሁመራና አካባቢዋ 700 ሺህ ኩንታል ለማገበያየት መታቀዱን ተናግራዋል፡፡