በጋምቤላ ክልል የሥራ እድል ፈጠራ ስራዎችን የሚመራ የዘርፍ ምክር ቤት ተቋቋመ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የሥራ እድል ፈጠራ ስራዎችን የሚመራ የዘርፍ ምክር ቤት ተቋቋመ
ጋምቤላ (ኢዜአ) ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም በጋምቤላ ክልል የሥራ እድል ፈጠራ ስራዎችን በተቀናጀ አግባብ ለመምራት የሚያስችል የዘርፍ ምክር ቤት ተቋቋመ። የተቋቋመው ምክር ቤት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ ሲሆን 57 ባለድርሻ አካላትን በአባልነት ያቀፈ ነው። በበጀት ዓመቱ ለ12 ሺህ 637 የክልሉ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱም በምክር ቤቱ መስራች ጉባኤ ላይ ተገልጿል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በመሰራች ጉባኤው ላይ እንደገለጹት ምክር ቤቱን ማቋቋም ያስፈለገው የሥራ እድል ፈጠራ ስራዎችን በተቀናጀ አግባብ በመምራት ዘርፉን ውጤታማ ለማደረግ ነው። በክልሉ ከእዚህ በፊት ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሲሰራ ቢቆይም ከሥራ አጡ ቁጥር አንጻር ሲከናወን የነበረው ሥራ በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ የተሻለ አደረጃጀት እንዲፈጠር መደረጉን ተናግረዋል። የተቋቋመው ምክር ቤት በዘርፍ የሚከናወኑ ስራዎችን በአግባቡና በተቀናጀ መልኩ በመምራት የወጣቱን ተጠቀሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንዲሰራም አቶ ኡሞድ አሳስበዋል። በበጀት ዓመቱ በሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በዕቅድ የተያዙ ወጣቶችን በሙሉ ወደሥራ ለማስገባት በትኩረት መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል ። የክልሉ የከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ደዋች ጋርኮት በበኩላቸው በክልሉ ካሁን በፊት በነበረው የሥራ እድል ፈጠራ ውስብስብ ችግሮች እንደነበሩ አመልክተዋል። በተለይም የወጣቶች የአንድ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በበቂ ቁሳቁስና የሰው ኃይል አለመደራጀት ዘርፉ ውጤተማ እንዳይሆን እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱን ለአብነት ጠቅሰዋል ። የተቋቋመው የምክር ቤት ችግሮቹን ሊፈታ እንደሚችል አመላክተዋል። ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ ኡኩኝ ኡኬሎ በሰጡት አስተያየት በበጀት ዓመቱ "የታቀደውን የሥራ ዕድል ፈጠራ ስኬታማ ለማድረግ የተጠናከረ የክትትልና የድጋፍ ሥራ መከናወን አለበት" ብለዋል። "ምክር ቤቱ በከተማና በገጠር የታለመውን የሥራ ዕድል ፈጠራ ውጤተማ ለማድረግ አደረጃጀቱን እስከ ቀበሌ በማውረድ መስራት ይጠበቅበታል" ያሉት ደግሞ የጉባኤው ተሳታፊ አቶ ድርሳን ወንድሙ ናቸው።