ቀጥታ፡

በሃዋሳ ድርጅታዊ ጉባኤ የውህደት ስምምነት ላይ ህወሃት ልዩነት የለውም…ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

ጥቅምት 13/2012 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ/ኢህአዴግ ባስተላለፈው የውህደት ሃሳብ ላይ ህወሃት ልዩነት እንደሌለው የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።

ሊቀመንበሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትላንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በሃዋሳው ድርጅታዊ ጉባኤ አባል ድርጅቶች ለውህደት በደረሱበት ስምምነት ላይ ልዩነት የለውም።

ድርጅቶቹ የፕሮግራም ልዩነት በወቅቱ እንዳልነበራቸው ያስታወሱት ዶክተር ደብረጽዮን በዚህም ለውህደት ተስማምተው የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ እንደቆዩ ተናግረዋል።

በፌዴራል መንግስቱ በሚተዳደሩት አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የነበሩ የአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች የሴቶች እና የወጣቶች ደረጃጀቶችን ወደ አንድ ለማምጣት በኢህአዴግ ሴቶች እና ወጣት ሊጎች አደረጃጀት ተግባራዊ መደረጉንም በማሳያነት ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ ያለው የተቀላቀለ የሃይል አሰላለፍ እና የፕሮግራም ለውጥ በሃዋሳ ከተላለፈው የኢህአዴግ ውሳኔ ፈጽሞ የተለየ በመሆኑ አባል ድርጅቶቹ በፕሮግራምም ሆነ በይዘት መለያየታቸው በገሃድ እየታየ መምጣቱን ዶክተር ደብረጽዮን አስረድተዋል።

የውህደት እንቅስቃሴው በስምምነቱ መሰረት እየተሰራበት ባለመሆኑና እየታየ ባለው የአሰላለፍ መደበላለቅ ምክንያት ህወሃት ውህደቱን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚቸገር ጠቁመዋል።

የዘንድሮ ምርጫን አስመልክቶም ካለፉት ጊዜያት በተሻለ ደረጃ የኢህአዴግና የመንግስት ቁርጠኝነት እየታየ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየሰጡዋቸው ካሉት መግለጫዎች መረዳታቸውን ተናግረዋል።

"ሆኖም ስለምርጫው የሚደረጉ የቅድመ-ዝግጅት ስራዎችም ሆኑ ምርጫ ቦርድ እስከ አሁን የጊዜ ሰሌዳ አውጥተው ሲንቀሳቀሱ አይታይም" ብለዋል።

በአንዳንድ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶም ሆነ በሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ በሀገራችን የተለያዩ ችግሮች ስላሉ እነሱ ሳይፈቱ ምርጫውን ማካሄድ አስቸጋሪ እንደሚሆን የሚሰጠው ገለጻም ትክክል እንዳልሆነ ገልጸዋል።

የምርጫው መካሔድ ተገቢ በመሆኑም ከሌሎች ስራዎች ጎን ለጎን በህገ-መንግስቱ መሰረት የማስፈጸሙን አስፈላጊነት ህወሃት እንደሚያምን በመግለጫቸው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም