በትግራይ ክልል ከ15 ሺህ በላይ ኤርትራዊያን ስደተኛ ተማሪዎች መደበኛ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል ከ15 ሺህ በላይ ኤርትራዊያን ስደተኛ ተማሪዎች መደበኛ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ
ጥቅምት 13/2012 ዓ.ም በትግራይ ክልል ከ15 ሺህ በላይ ኤርትራዊያን ስደተኞች መደበኛ ትምህርት በመከታተል ላይ መሆናቸውን የሰሜን ኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የኢትዮጰያ መንግስት ለ12 ኤርትራውያን ስደተኞች የከፍተኛ ትምህርት እድል መስጠቱ ታውቋል። በአስተዳደሩ የትምህርት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ኤፍሬም ሓጎስ ለኢዜአ እንደገለፁት በትግራይ ክልል መደበኛ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ያሉ ኤርትራዊያን ተማሪዎች በአራት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ስደተኞች ናቸው፡፡ ከ15 ሺህ በላይ ህጻናት ተማሪዎች መደበኛ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ያሉት በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በአዲ ሓሩሽ፣ በማይ ዓይኒ፣በህፃፅና በሽመልባ የኤርትራዊያን መጠልያ ጣቢያዎች በቅርብ ርቀት በተገነቡ ትምህርት ቤቶች ነው። ስደተኛ ተማሪዎቹ ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው ጋር አብረው በመማር ላይ መሆናቸውን አስተባባሪው ገልጸዋል። መደበኛ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ካሉት ኤርትራዊያን መካከልም አንድ ሺህ 761ዱ ሴቶች መሆናቸውን አቶ ኤፍሬም አመልክተዋል። ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ትምህርቱ እየተሰጠ ያለው በቅደመ መደበኛ፣ መደበኛና በሙያ ክህሎት ማበልፀጊያ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጰያ መንግስት በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ሦስት ሴቶችን ጨምሮ ለ12 ኤርትራዊያን ስደተኞች የከፍተኛ የትምህርት እድል መስጠቱን አስተባባሪው ተናግረዋል። የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስታት የፈጠሩትን ሰላም ተከትሎ የትምህርት እድሉ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማስቻሉን አቶ ኤፍሬም ገልጸዋል። ''የተፈጠረው የሰላም ስምምነትም በሁለቱም ህዝቦች መካከል የበለጠ መቀራረብና የመተሳሰብ ስሜት ከፍ እንዲል አስችሏዋል'' ብለዋል። የከፍተኛ የትምህርት እድል ካገኙት ኤርትራዊያን መካከል ወጣት ተስፋልደት መሓሪ እንዳለው የኢትዮጵያ መንግስት በሰጠው የትምህርት እድል እጅግ መደሰቱን ተናግሯል። የትምህርት እድሉ በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል የተጀመረውን መቀራረብ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ነው ያስታወቀው ወጣት ተስፋልደት። ሌላዋ የእድሉ ተጠቃሚ ወጣት ሜሮን መንግስትአብ በሁለተኛ አገሯ የከፍተኛ ትምህርት እድል ተጠቃሚ በመሆኗ ልዩ ስሜት እንደፈጠረባት ተናግራለች። ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ 350 ኤርትራዊያን ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ገብተው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችል። በዞኑ በሚገኙት አራቱ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ከ200 ሺህ በላይ ኤርትራዊያን ስደተኞች እንደሚገኙ ከዞኑ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።