ሙሳ ፋኪ የሩሲያ ባለሃብቶች በአፍሪካ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
ሙሳ ፋኪ የሩሲያ ባለሃብቶች በአፍሪካ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ ጥቅምት 13/2012 የሩሲያ ባለሃብቶች በተፈጥሮ ሀብቷ ምቹ በሆነችው አፍሪካ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጥሪ አቀረቡ። ሊቀመንበሩ ጥሪውን ያቀረቡት በሩሲያ ሶቺ ከተማ እየተካሄደ ባለው የሩሲያ-አፍሪካ የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ነው። የሩሲያ የግልና የመንግስት ኩባንያዎች አፍሪካ ላይ ኢንቨስት ቢያደርጉ ከታክስ ቅነሳ ጀምሮ ሌሎች ሁኔታዎች እንደሚመቻቹላቸው ሙሳ ፋኪ ተናግረዋል። ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ አፍሪካ የበርካታ የተፈጥሮ ሀብት በተለይም የማዕድንና የነፋስ ኃይል ባለቤት እንደሆነች ጠቅሰዋል። አፍሪካ ከኋላቀርነት በመላቀቅ፣ ልማትና ዴሞክራሲን ለማሳደግ ቆርጣ በመነሳት ስትራቴጂካዊ ስልቶችን ነድፋ እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኗንም ገልጸዋል። በመሆኑም ከሌሎች አህጉራትና አገሮች ጋር በመተባበር ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቷን ማጠናከር እንደምትሻ አብራርተዋል። የሩሲያ ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ በኃይል፣ በፈጠራ፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ በቴሌኮሙኒኬሽንና በሌሎችም መስኮች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል። አህጉሪቷ በእነዚህና በሌሎች ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ሊያፈሱ የሚመጡ ባለሀብቶችን ለመቀበል ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል። በተለይም የንፋስ ኃይል ኃይል የማመንጨት ሂደት ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጠው ገልጸው፤ ይህም አካባቢያዊ የአየር ንብረትና የስነ-ምህዳር ሚዛንን የሚጠብቅ በመሆኑ ይበረታታል ነው ያሉት። ሩሲያ አፍሪካ ከአፓርታይድ ነፃ እንድትወጣ ያደረገችው አስተዋጽኦ የማይዘነጋ መሆኑን የጠቀሱት ሙሳ ፋኪ በተጨማሪም ለበርካታ አፍሪካዊያን የህክምና፣ የዲፕሎማትነትና ሌሎች የማህበራዊ ሳይንስ ዘርፎች የትምህርት ዕድል በመስጠትና ውጤታማ በማድረግ ትልቅ ሚና ተጫውታለች ብለዋል። በቀጣይም አገሪቷ አፍሪካ ወደ ብልጽግና በምታደርገው ግስጋሴ አብራ እንደምትሰራ ያላቸውን እምነት ገልጸው በሁለቱ በኩል ያላቸውን ግንኙነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አክለዋል።