ሐይማኖታዊ መመሪያዎችንና እሴቶችን ለሰላምና ለአገር ግንባታ ማዋል ይገባል-ጉባዔው - ኢዜአ አማርኛ
ሐይማኖታዊ መመሪያዎችንና እሴቶችን ለሰላምና ለአገር ግንባታ ማዋል ይገባል-ጉባዔው
ሀዋሳ ጥቅምት 12 ቀን 2012 ሐይማኖታዊ መመሪያዎችና እሴቶችን ከመንፈሳዊ ሕይወት ባለፈ ለሰላምና ለአገር ግንባታ ማዋል እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አስገነዘበ። ጉባዔው ''የብሄርና የሃይማኖት ብዝኃነት አያያዝና አስተዳደር'' በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው የሰላም ኮንፈረንስ በሀዋሳ ተካሂዷል። የጉባዔው ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በኮንፈረንሱ ላይ እንዳሉት ተቋማቱ ያሏቸውን መመሪያዎችና እሴቶችን ለአገርና ለሰላም ግንባታ በማዋል ብዝኃነትን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል። እያንዳንዱ አማኝ የሃይማኖቱን መመሪያዎች በማክበርና በእሴቶቹ በመመራት ማህበራዊ ትስስሩንና አብሮነትን እንዲያጎለብትም ጠይቀዋል። ''ሃይማኖታዊ መመሪያዎችና እሴቶች መንፈሳዊ ህይወትን ከመገንባት ጎን ለጎን የሰዎችን ማህበራዊ ግንኙነትና አብሮነት በማጠናከር ዜጎች በአገር ሰላምና ግንባታ ሂደት የላቀ አስተዋጽኦ እንድናበረክት ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ ሚና አላቸው” ሲሉም ተናግረዋል። ብዝኃነትን በመቀበልና በማስተናገድ ሂደት ውስጥ ልዩነቶች አይነሱም ማለት እንዳልሆነ ያስረዱት ቀሲስ ታጋይ፣ ሐሳቦች እንዲንሸራሸሩ በመፍቀድ ብዝኃነትን ማስተናገድ እንደሚገባ ተናግረዋል። የሰላም ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ሀለፎም አባይ በበኩላቸው የሃይማኖት አባቶች ያላቸውን በኅብረተሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ለሰላም ግንባታ እንዲያውሉት ጠይቀዋል። ''ግጭትና የግጭት መንስኤዎችን በመቀነስ ብሎም በማስወገድ የኅብረተሰቡን ሰላም ለመጠበቅ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች ሁሉም የማህበረሰብ አካላትና መላው ሕዝባችን አገራዊና የዜግነት ኃላፊነታችሁን በተግባር የምትወጡበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንደምንገኝ ማስታወስ እወዳለሁ” ብለዋል። የደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ከበደ ፎከራ ክልሉ የበርካታ ብሄር/ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ ከመሆኑ አኳያ ተቻችሎ የመኖር ተምሳሌትነቱን እንዲያስቀጥል አሳሰበዋል። የሰላምን ጠቀሜታና አስፈላጊነት አውቆ ማህበራዊ መሠረትን አስፍቶ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በኮንፈረንሱ ላይ ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።