የኤሌክትሪክ አገልግሎት ይፋ ያደረገው የታሪፍ ማሻሻያ በደንበኞች ላይ ቅሬታን አስከትሏል - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ይፋ ያደረገው የታሪፍ ማሻሻያ በደንበኞች ላይ ቅሬታን አስከትሏል
ጥቅምት 12/2012 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ይፋ ያደረገው የታሪፍ ማሻሻያ የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃና አቅም ያገናዘበ አይደለም ሲሉ ተጠቃሚዎች ቅሬታ አቀረቡ። በኤሌክትሪክ አገልግሎት ተመን ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2011 ዓ.ም ለአራት አመት የሚቆይ የታሪፍ ማሻሻያ ማድረጉን የሚታወስ ነው። ባለፈው አመት የተደረገውን የታሪፍ ማሻሻያ ዘንድሮም እንደሚደግም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ማድረጉ ይታወቃል። ተጠቃሚዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ታህሳስ 2011 ወር ላይ ያደረገው የታሪፍ ማሻሻያና በቀጣይም ታህሳስ ወር የሚቀጥለው የታሪፍ ማስተካካያ የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃና አቅም ያገናዘበ አይደለም። የታሪፍ ማስተካከያው የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገባና የበዛ እንደሆነም ተናግረዋል። ማሻሻያው ቀደም ሲል ይከፍሉት ከነበረው ታሪፍ እስከ ሶስት እጥፍ እንዲከፍሉ ያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ማህበረሰብ ጫና ውስጥ እንዲወድቁ ያስገደደ መሆኑን ጠቁመዋል። መንግስትና ህዝብ የተሳሳረ በመሆኑ የህብረተሰቡን ችግር ዝቅ ብሎ በመመልከት የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃና አቅም ያገናዘበ ማስተካካያ መደረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ እንደገለጹት፤ 2011 ታህሳስ ወር ላይ የተደረገው የታሪፍ ጭማሪ የኃይል አጠቃቀምን መስራት ያደረገ ነው ። በዚህ ዝቅትኛ የኃይል ተጠቃሚዎች የዛሬን ገበያ ታሳቢ ያደረገው ጭማሪ እንዳይኖርባቸው በማድረግና ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙት ደግሞ ከፍተኛ ክፍያ እንዲከፍሉ መደረጉን ተናግረዋል ። የታሪፍ ጭማሪው አገራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትና የደንበኞች ብዛት ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍላጎት አንጻር ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠትና ለማስፋፋት የሚያስችል ገቢ ማግኘት ባለመቻሉ ማስተካከያው ማስፈለጉን አስረድተዋል።