ቀጥታ፡

መልካም ሥነ-ምግባር በመላበስ በትምህርታችን ውጤታማ ለመሆን ተዘጋጅተናል...የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች

ፍቼ (ኢዜአ) ጥቅምት 12 ቀን 2ዐ12 በትምህርት ቆይታቸው መልካም ሥነ-ምግባርን በመላበስ ውጤታማ ለመሆን መዘጋጀታቸውን የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ተናገሩ።

በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው ሕብረተሰብ የተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ከሌሎች ተማሪዎች ጋር አንድነታቸውን ለማጠንከር መነሳሳት እንደፈጠረባቸውም ተናግረዋል።

ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወደዩኒቨርሲቲው ተመድበው ለመጡ 1ሺህ 7ዐዐ የሚጠጉ ተማሪዎችና ወላጆች ከዛሬ ጀምሮ ደማቅ አቀባበል እየተደረገ ነው።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች መካከል ከአማራ ክልል ቡሬ ዳሞት ወረዳ የመጣችው ሔለን ስነሻው በተደረገላቸው አቀባበል ደስተኛ መሆኗን ተናግራለች።

"ወደአካባቢው የመጣሁበት ዋና ዓላማ እውቀት በመቅሰም ራሴንና ቤተሰቤን ለመርዳት በመሆኑ መልካም ስነምግባር በመላበስ በትምህርቴ ውጤታማ ለመሆን ጠንክሬ እሰራለሁ" ብላለች።

በዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎችና ለወላጆች የተደረገ ደማቅ አቀባበል ቀጣዩን የዩኒቨርሲቲ ቆይታዋን በፍቅርና በአንድነት ለማሳለፍ ተስፋ እንዳሳደረባት ገልጻለች።

በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ጠንክሮ በመስራት ለከፍተኛ ውጤት መዘጋጀቱን የተናገረው ከደሴ ከተማ የመጣው ሰለሞን ሽፈራው በተደረገለት አቀባበል ደስተኛ መሆኑን አመልክቷል፡፡

ተማሪዎች የሚኖራቸውን ማንኛውም ሀገራዊ ጥያቄ ለሰላምና ውይይት በር በሚከፍት መልኩ ማቅረብ እንዳለባቸውም አመልክቷል።

በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ከማንኛውም የጥፋት ተግባር ራሱን ገድቦ በትምህርቱ ውጤታማ ለመሆን እንደሚንቀሳቀስ የገለጸው ደግሞ ከምዕራብ ወለጋ ዞን የመጣው ተማሪ ሲያቅ ቦጋለ ነው።

በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው ማህበረሰብ የተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል በተማሪዎች መካከል መልካም ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግሯል።

ከተማሪ ወላጆች መካከል ወይዘሮ እክም ሞላ በበኩላቸው "ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎችና ለወላጆች ያደረገው ቤተሰባዊ አቀባበል ልጄ በቀጣይ ተረጋግቶ እንዲማር ተስፋ አሳድሮብኛል" ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ኘሬዚዳንት ዶክተር ገናነው ጐፌ በበኩላቸው ተቋሙ ዘንደሮ 1ሺህ 695 አዲስ እንዲሁም 2ሺህ 688 ነባር ተማሪዎችን ተቀብሎ በመደበኛ የትምህርት መርሀግብር እንደሚያስተምር ተናግረዋል።

የመማር ማስተማር ስራው ስኬታማ እንዲሆንም በቂ የመሰረተ ልማትና የሰው ኃይል አስቀድሞ እንዲሟላ መደረጉን ገልጸዋል።

ዶክተር ገናነው እንዳሉት በተለይ ባለፉት ዓመታት በተማሪዎች መካከል ይስተዋል የነበረው የእርስ በርስ ግንኙነት መሻከርና ያልተገቡ ድርጊቶች ዘንድሮ ለማስወገድ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።

"ተቋሙ በሥነ ምግባር የታነጹና የሥራ ባህል ያዳበሩ ወጣቶች መፍለቂያ እንዲሆን ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የውጭና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር የሺመቤት ቦጋለ ናቸው።

በተለይ ተቋሙን የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ በማድረግ ለሁከትና ጥፋት የሚዳርጉ ድርጊቶችን አስቀድሞ ለመከላከል ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣ ከአካባቢው ነዋሪዎችና ተማሪዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ተማሪዎች ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት በተቋሙ አሰራርና ህጐች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንደሚሰጥ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም