ቀጥታ፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሰራተኛ ማህበራት በበቂ ሁኔታ አልተደራጁም ተባለ

ጥቅምት 12/2012 በኢትዮጵያ ሥራ በጀመሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሠራተኛው መብት ጥብቅና የሚቆሙ ማኅበራት በበቂ ሁኔታ እንዳልተደራጁ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን አስታወቀ። የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን 18ኛው መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል። በጉባኤው መክፈቻ ላይ የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ እንዳሉት፤ አብዛኛዎቹ አሰሪዎች በየኩባንያዎቻቸው የሰራተኛ ማህበበር እንዲደራጅ ያላቸው ፈቃደኝነት ዝቅተኛ ነው። ይህም ሠራተኞች መብቶቻቸውን በተደራጀ መንገድ እንዳይጠይቁ እንቅፋት እየሆነባቸው ነው ሲሉ አቶ ካሳሁን አስረድተዋል። በአገሪቱ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ፀድቆ ስራ ላይ የዋለ ቢሆንም ሰራተኛን በማህበር በማደራጀቱ ሂደት ላይ የአሰሪና ሰራተኛ አለመግባባቶች ችግር እንደሆኑም ነው የተገለጸው። በተለይም ከመንግስት ወደ ግል የተዘዋወሩ ድርጅቶች ባሉባቸው የስራ ክፍተቶች ምክንያት የሚፈለግባቸውን ዕዳ ባለመክፈላቸው ምክንያት የሠራተኛው ዋስትና አደጋ ላይ እየወደቀ እንደሚገኝም አቶ ካሳሁን ያስረዳሉ። ስለሆነም ድርጅቶቹ በአገር ውስጥ ገቢ በመያዝ መንቀሳቀስ አለመቻላቸውንም በመጠቆም። ከዚህ በተጨማሪም የስራ ላይ አደጋን መከላከል እንዲቻል የጥንቃቄ አልባሳት ለሠራተኞች ባለመቅረቡ ምክንያት በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚደረጉ ግንባታዎች ከፎቆች በመውደቅ የሞትና የአካል ጉዳት እየተከሰተ እንደሚገኝም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። ይሄ ከፍተኛ ችግር በመንግስትም በኩል ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ አቶ ካሳሁን አሳስበዋል። በቀጣይ ኮንፌዴሬሽኑ ያልተደራጁ ሰራተኞችን በማህበር የማደራጀቱን ስራ በዘመቻም ሆነ እንደመደበኛ ስራ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል። የአለም ስራ ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት አመራሮችን ያካተተ ሰራተኛን ማደራጀት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ አገር አቀፍ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ እንደሆነ በዚሁ ጊዜ ተገልጿል። ይሄን እንቅስቃሴ ተከትሎ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሰራተኛው መደራጀት እንዳለበትና ህገመንግስታዊ መብቱ እንደሆነ ለአሰሪዎቹ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየሰራ እንደሚገኝም አቶ ካሳሁን ተናግረዋል። የአሰሪና ሰራተኛ አማካሪ ቦርድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ ከትኩረት አቅጣጫዎቹ አንዱ እንደሆነም ተገልጿል። የኢፌዴሪ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው ''የአሰሪና ሰራተኛ ስምሪት ህብረተሰቡን ከድህነት ለማውጣትና አገርን ወደ ተሻለ እድገት የሚያመጣ የላቀ ተግባር ነው'' ብለዋል። አሰሪዎች ለሰራተኛው ስራና ትጋት ድጋፍ  በማድረግ ለተሻለ ውጤት እንዲሰራ የሚያስችል ስርዓት ዘርግቶ የሰራተኛውን አቅም መገንባት ላይ ትኩረት እንዲያደርግ አሳስበዋል። የደመወዝ ወለልን በተመለከተም አዋጁ የወጣ ሲሆን ቦርድ ተቋቁሞና በቂ ጥናት ተደርጎ በቀጣይ ወደ ስራ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም